የሞያሌ ከተማ ግጭት መቀስቀሱ ተነገረ

Bilderesultat for ethiopian moyale city

ኢትዮጵያ ሶማሌ እና የኦሮሚያ ክልሎች በሚዋሰኑባት የሞያሌ ከተማ ግጭት መቀስቀሱ ተነገረ። በሞያሌ ሆስፒታል የሚሠሩ ባለሞያዎች በከተማዋ በነበረው የተኩስ ልውውጥ ሦስት ሰዎች መሞታቸውን እና ከ20 በላይ መቁሰላቸውን ተናግረዋል። አንድ የከተማዋ ነዋሪ ግጭቱ በገሪ ሶማሌ እና በቦረና ኦሮሞ መካከል የተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሁለት የተማዋ ነዋሪዎች የተኩስ ልውውጡ እስከ ማምሻ መቀጠሉን አረጋግጠዋል። ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ የተኩስል ልውውጡ መጀመሩን የሚናገሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የመንግሥት ሠራተኛ ” ተኩስ የነበረበት ከቴሌው እና ከባንኩ ጀርባ አካባቢ ነው። ከመናኻሪያው ጀርባም ከባድ የሆኑ መሳሪያዎች እየተተኮሱ ነው ያሉት። ከዚህኛውም ወገን እየተተኮሰ ነው ያለው” ሲሉ አስረድተዋል። በሞያሌ ከተማ ሆስፒታል የሚሰሩ አንድ ባለሞያም የተኩስ ልውውጡ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ መጀመሩን አረጋግጠው ሦስት ሰዎች መሞታቸውን እና ከ20 በላይ መቁሰላቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የመንግሥት ሠራተኝ ነኝ ያሉን የሞያሌ ነዋሪ በከተማዋ «ለመንቀሳቀስ በጣም ከባድ ነው። በአጠቃላይ ግን ያስፈራል» ሲሉ ተናግረዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች በየቤታቸው መሸሸግ መምረጣቸውን የተናገሩት የዐይን እማኙ «እስካሁን ድረስ መንግሥት የሚወስደው እርምጃ ምን እንደሆነ አልታወቀም። ምንም እየወሰደ አይደለም» ሲሉ ተናግረዋል። ከተማዋ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደማይታይባት፣ የስልክ አገልግሎት መቆራረጥ እየገጠማቸው መሆኑን የተናገሩት የዐይን እማኙ ነዋሪዎች ሥጋት እንደተጫናቸው አስረድተዋል። በዚህ ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የኦሮሚያና የሶማሌ መሥተዳድሮች አስተያየትን ለማከተት ያደረግንው ጥረት አልተሳካም።

%d bloggers like this: