ለጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን… ከ ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት;

ሰላም ክቡር ሚኒስቴር፤


ህዝብዎ ባለፈው ባደረገው ምርጫ እርሶ የማይፈልጉትን መምረጡን ተከትሎ ስልጣንዎን ሊለቁ እንደሆነ በሰማን ግዜ በውነት ተደነቀን….
ለዚህ እኮ ነው እናንተ አውሮፓውያን ሁሌም የምትገርሙን፤ ሰልጠነናል አውቀናል ትላላችሁ እንጂ ገና ብዙ ይቀራችኋል። ሲጀመር ህዝቡ ድምጽ የሰጠው እርስዎ ከስልጣንዎ እንዲለቁ አይደለም፤ ቢሆንስ የምን ለህዝብ ፊት መስጠት ነው… በእንዲህ ያለው ሆድ የሚያስብስ ጊዜ የሚባለው ‘’ድርጅቴ ከፈቀደልኝ ስልጣኔን እለቃለሁ’’ ነው… ከዛ ስልጣንዎን ባይለቁም ድርጅታቸው አልፈቀደም ማለት ነው ይባላል።
ከሁሉ ከሁሉ ግን ህዝቡ ምን ሆንኩኝ ብሎ ነው እርስዎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማይፈልጉትን እና ያልደገፉትን ነገር የሚፈልገው። አንዴ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ እርስዎስ ህዝብን ማማከር ብሎ ፈሊጥ ከየት አመጡት? ዝም ብለው ያሻዎትን ወስነው ሲያበቁ… ህዝቡ እንዴት… ብሎ ሲጠይቅዎ ‘’ይሄንን ጉዳይ ለዚህ ህዝብ የማሳወቅ ግዴታ ያለብኝ አይመስለኝም።’’ ይባላል እንጂ ህዝብን ወስን ብሎ መጥራት ነውር አይደለም እንዴ…
እርግጥ ነው ህዝብ ባለጌ ነው አንዳንድ ጊዜም ሆ ብሎ ተቃውሞ ያስነሳ ይሆናል… ይሄንን መከላከል ታድያ ከባድ ነው ሊሉ ይሆናል እኮ… የሽብርተንነት አዋጅ አላችሁ አይደል እንዴ… እኛ ራሳችን እኮ አዋጁን ከናንተ ነው ቀጥታ ቃል በቃል የቀዳነው… ታድያ ከቃልዎ የሚያፈነግጠውን ሁላ ያፈነገጠውን ብቻ ሳይሆን ያሰበውን ሳይቀር የሽብርተኝነት አዋጁን እየጠቀሱ መጠፍነግ ሲችሉ… የምን ለህዝብ ፊት መስጠት ነው…. ?
እሺ እምቢኝ ብለው አንዳንድ ነውጠኞች ስራዎን ተቃውመው አደባባይ ወጡ እንበል… እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥም በመጀመሪያ ደረጃ ማድረግ የሚገባዎ ሌሎች የርስዎ ደጋፊዎችን በቴሌቪዥን ጣቢያዎ አቅርበው ‘’አንዳንድ ጸረ ሰላም ሃይሎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልካም ሃሳብ መቃወማቸው ተገቢ አለመሆኑ ተገለጸ’’ የሚል ዜና ማሰራት። (እንደውም የምን መልካም ሃሳብ ራዕይ ይበሉት እንጂ…) አዎ ‘’የጠቅላይ ሚኒስትሩን ራዕይ… (እንደውም የምን ጠቅላይ ሚኒስትር ብሎ ማቃለል ነው… (የታላቁን መሪ ይበሉት… ) አዎ ‘’አንዳንድ ጸረ ሰላም ሃይሎች የታላቁን መሪያችንን ራዕይ ለማደናቀፍ መሞከራቸው ተገቢ አለመሆኑን የለንደን ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ አክለውም ይህንን ታላቅ ራዕይ ለማደናቀፍ እና ህገ መንግስቱን በሃይል ለመናድ የሚሞክሩ የሻቢያ ተላላኪዎች ላይ መንስግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን… ብለዋል።’’ ብሎ ዜና ማሰራት። (ያው የሻቢያ ተላላኪ ያልንልዎ ከተቸገሩ ይጠቀሙበት ብለን ነው ሰርተው ይከፍላሉ። የራስዎ ተላላኪ ሲያገኙ ይመልሳሉ) እኛ ኦነግ ኦብነግ ግንቦት ሰባት እና ሌሎችም ስላሉን ችግር የለውም።
ከዛ ህዝቡ በዜና እርምጃ ይወሰድ ብሎ የለ… በቃ በነጋታው ስናይፐር የያዘ ወታደር አሰማርቶ ለተቃውሞ የወጣውን ሁላ ጠብ ጠብ… ማድረግ ነው።
ህዝብ ደም ካየ ይሸሻል። ጸጥ ይላል። ግፋ ቢል አንድ አራት መቶ አምስት መቶ ሰው ቢገድሉ… በቃ… የተቀረው ህዝብ ዝም ይላል… ከሁሉ ከሁሉ ደሞ ህዝቡ ራስ በራሱ እንዲጠባበቅ የማድረግ ዘዴን መጠቀም አለብዎ… ይሄንንም እኛ ድሮ እና ከናንተ እና ከጥሊያን ነበር የተማርነው እርስዎ ዛሬ እንዴት ይሄ እንደጠፋዎ ገርሞናል።
የምዕራቡ አካባቢ ሰው በሃሳብዎ ያልተስማማ እንደሆነ ለሰሜኑ ህብረተሰብ ‘’የድሮን ስርዓት ሊያመጡብህ ነው…’’ ወይም ደግሞ ‘’ሃገሪቷን ሊበታትኑ አስበው ነው እና ህዝብ ሆይ በንቃት ጠብቅ’’ ብሎ ህዝቡ ራስ በራሱ እንዲጠባበቅ ማድረግ ጥሩ መላ ነው። ለስንቱ ወታደር አቁመው ይዘልቁታል።
የሆነው ሆኖ ግን ግራም ነፈሰ ቀኝ፤ ጠቅላይ ሚኒስትቴርነት ዝም ተብሎ የሚለቀቅ ስልጣን አይደለም። እኛ ሃገር መጥተው ልምድ ቢቀስሙ ሃያ አምስቱንም አመት አንድ መሪ ብቻ ይዘን ያገኙናል። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለፈው ሰሞን ‘’ድርጅቴ ከፈቀደ ስልጣን እለቃለሁ’’ ብለው አስደንገጠውን ነበር… (አዩ አይደል እንዲህ ነው የሚባለው….) ይሄው ድርጅታቸው ስላልፈቀደ አሁንም ድረስ ሞተው ሁላ ስልጣን አለቀቁም።
እና ክቡር ዴቪድ ካሜሮን በትንሽ ነገር ተከፍተው ስልጣን ለቃለሁ በማለት ለኛ ህዝብም ክፉ ነገር ባያሳዩብን መልካም ነው… አሁንም ያስቡበት እና ‘’ድርጅቴ አለቅም አለኝ…’’ ብለው ስልጣንዎን ያጥብቁ እኛ ላይም ትችት አያምጡብን.. ለነገሩ እኛጋ ሁሉ ነገር በህግ ነው… በአዲሱ የኮምፒውተር ደህነነት ጥበቃ አዋጅ ስም ማጥፋት የሚያስከስሰውን ክስ ደፍሮ የሚተችን ካለ ይሞክረን።
ከሁሉ ግራ የገባን ቆይ አቃቤ ህጎቻችሁ ፣ ፖሊሶቻችሁ እና ባጠቃላይ የጸረ ሽብር ግብረ ሃይሎቻችሁ ምን ሰርተው ሊበሉ ነው። ከርሶ ሃሳብ ውጪ የሆኑትን አስራ ሰባት ሚሊዮን ሰዎችን ሽብርተኛ ብሎ መፍረድ ያልቻለ ፍርድ ቤትስ ምኑን ፍርድ ቤት ተባለው….

በእውነት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ደግ አልሰሩም! ለማንኛውም ያስቡበት።

Posted By-Lemlem Kebede

Advertisements