በኦሮምያ ተቃውሞው ለ3ኛ ቀን ቀጥሎ ዋለ። በደቡብ በወልቂጤ ለ2 ቀናት የሚቆየው የስራ ማቆም አድማ ዛሬ ተጀም

በኦሮምያ ተቃውሞው ለ3ኛ ቀን ቀጥሎ ዋለ
በደቡብ በወልቂጤ ለ2 ቀናት የሚቆየው የስራ ማቆም አድማ ዛሬ ተጀምሯል
(ኢሳት ዜና የካቲት 7 ቀን 2010ዓ/ም) በኦሮምያ ክልል በተለያዩ ከተሞች የሚካሄደው ተቃውሞ ዛሬም ለ3ኛ ቀን ቀጥሎ ውሎአል። በአዳማ ከእስር የተለቀቁትን የኦፌኮ ምክትል ሊ/መንበር አቶ በቀለ ገርባም ለመቀበል በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ ድጋፉን ገልጿል። አገዛዙን የሚያወግዙ መፈክሮችም ተሰምተዋል። ወጣቶቹ የኢትዮጵያ ህዝብ ደም ደማቸው መሆኑን፣ ቄሮ ኢትዮጵያን ለማቋቋም ነው እንጅ ለመገንጠል አይደለም” የሚሉ አንድነትን የሚሰብኩ መፈክሮችን ሲያሰሙ ውለዋል።
በአዲስ አበባ አጎራባች ከተሞች በተለይም በወለቴ፣ ሰበታና ለገጣፎ ወጣቶች “ እንዲህ ነን” እያሉ ሲጨፍሩ አገዛዙን ሲያወግዙ ውለዋል።
በወሊሶ ህዝቡ ወደ ስታዲየም በመትመም “መንግስት ስልጣኑን ይልቀቅ፣ ፍትሀዊ ምርጫ ይደረግ” የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች ተሰምተዋል።
በምስራቅ ወለጋ ዞን አንገር ጉቴ ከተማ “የአማራ ደም የእኛ ደም ነው፣ የኦሮ ደም የእኛ ደም ነው በቀለ ገርባ እንደተፈታው ሁሉ ኮሎኔር ደመቀ መኮንንም ይፈታ” የሚሉ መፈክሮች ተሰምተዋል፡፡ ሁሉም እስረኞች ካልተፉ ግን ተቃውሞው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በሞጆ ደግሞ የገጠሩ ህዝብ ወደ ከተማ በመግባት ተቃውሞ ሲያሰማ ውሎአል።
በድሬዳዋ በነበረው ተከታታይ ተቃውሞ የፌደራል ፖሊሶችና የመከላከያ አባላት 4 ሰዎችን የገደሉ ሲሆን፣ ህዝቡ ለቀብር ሲወጣ “ እኛ በምንላችሁ ቦታ እንጅ እናንተ በመትፍለጉት ቦታ አትቀብሩም” በማለታቸው በህዝቡና በፖሊሶች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ነበር። ሁለት የፖሊስ መኪኖችም ተገልብጠው እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በወልቂጤ ዛሬ ለሁለተኛ ቀን የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ ተጀምሯል። አድማው ከዚህ ቀደም የቀረቡ የማህበራዊና አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ባለመፈታታቸው የተጀመረ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪዎች፣ ዛሬ ሁሉም የንግድ ድርጅቶች መዘጋታቸውንና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ አለመኖሩም ገልጸዋል። ጥያቄያቸው በአፋጣኝ ካልተመለሰ ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎችን እንደሚያዘጋጁ አስተባባሪዎች ገልጸዋል

Advertisements