ማኅበረ ቅዱሳን የፓትርያርኩ ክሥ የእውነት ጠብታ የሌለበት እጅግ ከባድ አደጋ እንዳለው ገለጸ

የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ኹኔታ ያሰጋው ማኅበረ ቅዱሳን የፓትርያርኩ የክሥ መመሪያ የእውነት ጠብታ የሌለበት እጅግ ከባድ አደጋ እንዳለው ገለጸ
– ቅዱስ ሲኖዶስ እርምትና አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥበት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ተማፅኗል
– ከኑፋቄ፣ ከአስተዳደር በደል እና ከዝርፊያ የተነሣ የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ኹኔታ አስግቶታል
ቅዱስ ሲኖዶስ እርምትና አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥበት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ተማፅኗል ከኑፋቄ፣ ከአስተዳደር በደል እና ከዝርፊያ የተነሣ የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ኹኔታ አስግቶታል በማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ የፓትርያርኩ አካሔድ “እንግዳ እና አስገራሚ ነው” ብሏል በአካልና በግለሰቦች በኩል እንዲኹም በደብዳቤ 6 ጊዜ ለውይይት ቢጠየቁም ፈቃደኛ አልኾኑም በፓትርያርኩ ስም የሚጻፉ ደብዳቤዎች ክብርና ተኣማኒነትያላቸው ይኾኑ ዘንድ አመልክቷል አግባብነት ያለው ወቅታዊ እርምትና መተማመኛ ያለው አሠራር ተግባራዊ እንዲኾን ጠይቋል
* * * (ሰንደቅ፤ ረቡዕ፤ ጥር ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.) – የማኅበረ ቅዱሳን ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆች ውስጥ በስውር የሚካሔደውና ለቤተ ክርስቲያንን የህልውና ስጋት የኾነው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ አሳሳቢ ደረጃ ስለ መድረሱ በተከታታይ መዘገቡን ተከትሎ፣ ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የማያቋርጥ ትግል እንዲካሔድ ለኮሌጆቹ ያስተላለፉት የክሥና የቅስቀሳ መመሪያ፣ አንዳችም የእውነት ጠብታ በሌለው መረጃ ላይ የተመረኮዘና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆቹን ክሥ የሚያስተጋባ እንደኾነ ማኅበሩ ገለጸ፡፡ ማኅበሩ፥ ትላንት ጥር 24 ቀን 2008 ዓ.ም.፣ በቁጥር ማቅሥአመ/239/02/ለ/08 ለፓትርያርኩ፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአድራሻ በጻፈውና ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱና ለተለያዩ መንግሥታዊ አካላት ደግሞ በግልባጭ ባሳወቀው ደብዳቤ፤ ለፓትርያርኩ የክሥና የቅስቀሳ መመሪያ በስፋት ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ማኅበሩ በዚኹ ምላሹ፣ ፓትርያርኩ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 2007 ዓ.ም. ምልዓተ ጉባኤው ያሳለፈውን ውሳኔ መሠረት አድርገው፣ “መናፍቃንና የተሐድሶ አራማጆች በቤተ ክርስቲያናችን ኮሌጆች ተምረው ስውር ዓላማቸውን በማካሔድ ሕዝበ ክርስቲያኑን በመከፋፈል ላይ ስለሚገኙ ከኮሌጆቻችን ጀምሮ … በማስረጃ የተደገፈ ጥናት እንድታቀርቡ” በሚል አጽንዖት ችግሩን እንዲያጠና ለተቋቋመው ኮሚቴ ኅዳር 4 እና 11 ቀን 2007 ዓ.ም የጻፉትን ደብዳቤ ለትውስታ ጠቅሷል፡፡ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ መረጃም፣ የሊቃውንት መፍለቂያ በኾኑት ኮሌጆች ላይ ስለ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ እንቅስቃሴ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ላይ የተመሠረተና ችግሩም በአጠቃላይ አሠራር ደረጃ እንዲፈታ የኹሉም የቤተ ክርስቲያን አካላት የነቃ ተሳትፎ እንዲያስፈልግ ለማስገንዘብ የተዘጋጀ እንጂ ከሣሾቹ እንደሚሉት፣ ኮሌጆቹን በጅምላ በሃይማኖት ሕጸጽ ለመወንጀል አልያም የግለሰቦችን ስም እየጠቀሱ ለማውጣት እንዳልቀረበ አስረድቷል፡፡
“እንደ እውነቱ ከኾነ፣ በጋዜጣው ላይ የወጣው አጠቃላይ የጽሑፉ ጭብጥ ሲታይ ቅዱስ ሲኖዶስ ከወሰነው ውሳኔ የተለየ ስምዐ ጽድቅ የጻፈችው ምን አለ?” ሲል የጠየቀው ማኅበሩ፣ በኮሌጆቹ አስተዳደር፣ ሠራተኞች፣ መምህራንና ደቀ መዛሙርት ስም የቀረበው አቤቱታ፣ ጋዜጣው በይፋ ያወጣው መረጃ፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በእውነተኛ የቤተ ክርስቲያን አካላት ዘንድ ትኩረት በማግኘቱ የተደናገጡት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች የሰርጎ ገብ እንቅስቃሴያቸው እንዳይገታባቸው የፈጠሩት የማዘናጊያ ውንጀላ እንደኾነ አብራርቷል፡፡ “ከየኮሌጆቹ ከሚማሩ ደቀ መዛሙርት መካከል በውድም ኾነ በግድ እንዲፈርሙ ተደርገው ለቅዱስነትዎ የቀረበልዎት ጥያቄ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነው ውሳኔ መኾኑ ተዘንግቶና የማኅበረ ቅዱሳን አንድ ተወካይ እንኳ ተገኝቶ ማብራሪያ እንዲሰጥ ሳይደረግ እንዲኽ ዓይነት ብያኔ በርስዎ በቅዱስ አባታችን መሰጠቱ አሳዝኖናል፤” ሲል ቅሬታውን ገልጧል፡፡ አያይዞም፣“ጥቂት የተሐድሶ እምነት አራማጆችን በርቱ፣ ተቃውሟችሁንና ማደናገራችሁን ቀጥሉበት የሚል የሚመስል መልእክት የያዘ ሐሳብ በቅዱስነትዎ ፊት መሰጠቱም እጅግ አስደንቆናል፡፡ በጥሞና ከታየ የቀረበውን መረጃ ወስዶ በቅዱስ ሲኖዶስ እንደገና የተቋቋመው ኮሚቴ እንዲያጠናው ማድረግ የሚገባ እንጂ ሊያስከሥሥም ኾነ እንዲኽ ዓይነት ደብዳቤ ሊያስጽፍ የሚችል ነገር ለመኖሩ በፍጹም አልታየንም፤” ሲል የፓትርያርኩ አካሔድ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔና አሠራር የሚቃረን፣ ማኅበሩን የማይገልጽና ፍትሐዊነት የጎደለው እንደኾነ ተችቷል፡፡ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን የእምነት መግለጫቸውን አሳትመው በይፋ በማሠራጨት የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርተ ሃይማኖትና ቀኖና በማንአለብኝነት በሚፃረሩበት፤ በአስተዳደራዊ መዋቅራችን ውስጥ ጥቅመኝነት ክብር ተሰጥቶት በግላጭ ዝርፊያ በሚፈጸምበትና አገልጋይ ካህናት በየቦታው በሚበደሉበት በአኹኑ ወቅት፤ በርእሰ መንበሩ ደረጃ ለቤተ ክርስቲያን የማይበጁ እንዲኽ ያሉ የሐሰት ክሥና የቅሰቀሳ መመሪያ ያዘሉ ደብዳቤዎች እየተፈረሙ ሲወጡ ማየት እጅግ ከባድ አደጋ እንዳለውም ማኅበረ ቅዱሳን በደብዳቤው አሳስቧል፡፡ ክሡን በግልባጭ እንኳ እንዲያውቀው አለመደረጉንና የደብዳቤው ዓላማና ተልእኮው ምን እንደኾነ ለመገመት መቸገሩን የገለጸው ማኅበሩ፤ ምንም እንኳ ማኅበሩን፣ አጥጋቢ ሥራ ሠርቷል ወይም አልሠራም፤ ስሕተቶችን ይፈጽማል አይፈጽምም ብሎ መከራከር፣ መውቀስና በሐሳቦቹም መወያየት፣ አስፈላጊም ሲኾንም መገሠጽ እየተቻለ ከአንድ ቅዱስ አባት ቀርቶ ከየትኛውም የተቋም ሓላፊ በማይጠበቁና የሰዎችን ስሜት በሚያስቆጡ ቃላት መሸንቆጥ በእጅጉ አሳዝኖኛል፤ ብሏል፤ በተለይም “የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት እየፈጸመ ይገኛል” የሚለው የፓትርያርኩ ጭፍን ብያኔ ለማኅበሩ አመራርና አባላት ቀርቶ ደብዳቤውን በየሚዲያዎቹ ያዩት ኹሉ፣ ትዕግሥትን የሚፈትን እንደኾነ እየገለጹለት እንደሚገኙም ጠቁሟል፡፡ አባታዊ መመሪያና ቡራኬ ለመቀበል፣ ለቤተ ክርስቲያን ቅን የማያስቡ አካላት በሚያነሡበትም ክፉ ጉዳዮች ለመወያየት÷ በአካል በመቅረብ፣ ለስድስት ጊዜያት ደብዳቤ በመጻፍ እንዲኹም ብፁዓን አባቶችን ጨምሮ በተለያዩ ግለሰቦችና አካላት በኩል ፓትርያርኩን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ጊዜ ሰጥተው ሊያወያዩት እንዳልቻሉ ማኅበሩ በጽሑፍ ምላሹ አውስቷል። በአንጻሩ ማኅበሩን በመክሠሥ ለሚቀርቡ የተለያዩ አካላት ፓትርያርኩ ጊዜ እየሰጡ እንደሚያነጋግሩ የጠቀሰው ደብዳቤው፣ “ለአንድም ቀን እንኳን በተከሠሥንበት ጉዳይ ቀርበን ቃላችንን እንድንሰጥ አለማድረግዎ አስደንቆናል፤” ብሏል። የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች በሚያዘጋጇቸውና በሚመሯቸው ድረ ገጾችና ብሎጎች ማኅበሩን ለመክሠሥ የሚያወጧቸው ሐሳቦች በፓትርያርኩ መመሪያም ተጠቅሰው መታየታቸው እንዳሳዘነውና እንዳስገረመው ማኅበሩ ገልጾ፣ ከሣሾች ባቀረቡት ቃል ላይ ብቻ ተመሥርቶ ፍርድ መስጠት እውነተኛውን ሕግ በምትተረጉመው ቤተ ክርስቲያናችን ፍጹም እንግዳ ሥርዓት ነው፤ ሲል ተችቷል፡፡ እውነታውን ለማወቅና ለሚነሡ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የጉዳዩን ባለቤቶች ጠርቶ ፊት ለፊት በማነጋገርና በመመካከር መፍታት እንጂ አንድ ጩኸት በተሰማ ቁጥር ደብዳቤ መጻፉ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንደማይበጅም ማኅበሩ አስገንዝቧል። ላለፉት 23 ዓመታት፣ በብፁዓን አባቶች ቡራኬና መመሪያ ሰጪነት፣ በገዳማውያን ጸሎትና በምእመናን ከፍተኛ ድጋፍ ቤተ ክርስቲያንን በአገልግሎቱ ለማገዝ ላለፉት 23 ዓመታት የዐቅሙን ያህል ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የጠቀሰው ማኅበሩ፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃንንና የአማሳኞችን ውንጀላ የሚያስተጋባው የፓትርያርኩ የክሥና የቅሰቀሳ መመሪያ በቅዱስ ሲኖዶስ በአንክሮ ውይይት ተካሒዶበት እርምት እንዲደረግበትና አስቸኳይ መፍትሔ መፍትሔም እንዲሰጠው ያደርጉ ዘንድ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ተማፅኗል፡፡ በፓትርያርኩ ስም የሚጻፉ ደብዳቤዎች፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚወክሉና ክብርዋን የሚያስጠብቁ፣ በኹሉም አካላት ተኣማኒነት ኖሯቸው ትኩረት ሰጥተው የሚመለከቷቸው እንዲኾኑ ማኅበሩ አስተያየቱን አስፍሮ ለወደፊቱም፣ አግባብነት ያለው ወቅታዊ እርምትና መተማመኛ ያለው አሠራር ተግባራዊ እስካልኾነ ድረስ፣ “የሚከተለው አደጋ ትልቅነት ይታየናል፤” ሲል የፓትርያርኩ ወገንተኛና ያልተስተዋለ(እየገነገነ የቀጠለ ኢ-ፍትሐዊና ዓምባገነናዊ አካሔድ) የከፋ መዘዝ እንዳያስከትል በደብዳቤው አስጠንቅቋል፡፡
Posted By-Lemlem Kebede
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s