የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው እንዴ? የዴምሕቶቹ የማነ እና ፍሰኃ (ደምስ በለጠ)

የዴምህት መስራች ፍሰሃ ሃይለማርያም

ከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ

ከ1998 እስከ 2000 እ.ኤ.አ የቆየው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በሻእቢያና በወያኔ መካከል ከፍተኛ ክፍተት ፈጥሮ እንደቆየ አሁንም መፍትሄ ያላገኘ ጉዳይ እንደሆነ ሁላችሁም የምታውቁት ነው። ከ1991 ሻእቢያ ኤርትራን ከተቆጣጠረ በኋላ በነበሩት ሰባት አመታት ሻእቢያዎች በኢትዮጵያ ላይ አንሰራፍተውትና ቀጣይ መዋቅር አሰናድተውለት የነበረውን የኤኮኖሚ ሲስተም ጦርነቱ ንዶታል ። ከዚያም በኋላ የሰዎች ልጆች ህይወት ተመሳቅሏል፤ ትዳር ፈርሷል፤ ልጆች ተበትነዋል ፤ የነበረው እንዳልነበረ ሆኗል ።

ዛሬ የማነሳው የየማነ ድምፁንና የፍስኃ ኃ/ማርያምን እጣ ነው። ሁለቱም የዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ሕዝቢ ትግራይ (ዴምሕት) መሪዎች የነበሩ ሰዎች ናቸው። መጀመሪያ የማነ ማነው? አሁንስ የት ደረሰ?

የማነ ድምፁ በወያኔ የትግል ዘመን የወያኔ ተዋጊ ሆኖ ከደርግ ጋር በተደረጉ ውጊያዎች ላይ ውሏል፤ ወታደር ነበር ። ወያኔ አዲስ አበባን ከጠቆጣጠረና ከተረጋጋ በኋላ ከሰራዊቱ ካሰናበታቸው የመጀመሪያ ሰዎች ውስጥ አንዱ ሆነ ። በስንብቱ ጊዜ ከውጊያ ልምድ በቀር፤ ሌላ የሚያውቀው የሙያ ስራ እውቀትም ሆነ ስልጠና አልነበረውም ። ከስንብት በኋላ መተዳደሪያ ስላልነበረው ከኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ቀደም ብሎ ስራ ለመፈለግ ወደ ኤርትራ ገብቷል።

ምፅዋ ሲገባ ሊያገኝ የቻለው በቀን ሰራተኝነት ኑሮውን መግፋት ብቻ ይሆናል ። በጦርነቱ የፈራረሰችው ምፅዋ እንደገና ስትታደስ የማነ በጉልበት ሰራተኝነት አገልግሏል ። ከዚህ ሌላ በወደብ እቃ በመጫንና በማራገፍም ሰርቷል ። እሱ ብቻ አልነበረም በዛ ያሉ የትግራይ ተወላጆች እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን እንዲሁ ኤርትራ ውስጥ ይሰሩና ይኖሩ ነበር ። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ይነሳል ። የጦርንቱ መነሳት እነዚህን ሰዎች በያሉበት ተቀርቅረው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል።

በአብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው የኤርትራ ከተሞች ሁሉ ልዩ እስር ቤቶች እየተዘጋጁ ታጉረዋል ። በዚያም ከፍተኛ የሆነ ስቃይ ረሃብና ጥማት ይደርስባቸው እንደነበር ባለፉት ፅሁፎቼ በዝርዝር አስቀምጫለሁ ። የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች አንድነት ድርጅት (ኢዴኃአድ) በኋላ ላይ የአርበኖች ግንባር የሚሆነው ድርጅት ፤ በየእስር ቤቱ ታጉረው ከነበሩት ኢትዮጵያውያን ወስጥ የአባላት ምልመላ ሲጀምር ከተመለመሉትና ወደ ሐሬና ለስልጠና ከተወሰዱት ሰዎች ውስጥ የማነ ድምፁ አንዱ ነበር ። ወታደራዊ ልምድ ስላለው በዚሁ ድርጅት ውስጥ የአንድ ጋንታ ሹምና የፖለቲካ ጉዳይ ሃላፊ ሆኖ ተመደበ ።

በቀደሙት ፅሁፎቼ ላይ እንደገለፅኩት ሻእቢያ የትግራይ ተወላጆችን ከሕብረ-ብሔር ድርጅቶች ውስጥ እየለቀመ ሲያወጣ ከተወሰዱት ሰዎች ውስጥ አንዱ ሆነ ። እነዚህን የትግራይ ተወላጆች ሻእቢያ ለብቻ ወስዶ ለአምስት ወራት በልዩ ካምፕ ውስጥ ስልጠና ሰጥቷቸው ፤ ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይ (ዴምህት) ብሎ ለብቻ አደራጃቸው ። በዚህ አይነት የማነ ድምፁ የመጀመሪያው የ(ዴምህት) መስራችና መሪ ይሆናል ። የካቲት 11 ቀን 1993 ዓ.ም ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይ (ዴምሕት)ን በሻእቢያ ደጋፊነት ያቋቁማል ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የወያኔ የደህንነት አባልና ሹም የነበረ ፍስኃ ኃ/ማርያም የሚባል ግለሰብ ወያኔን ከድቶ ወደ አስመራ ይታጠፍና ለሻእቢያ ለመስራት ይዋዋላል ። ሻእቢያም ወዲያውኑ ፍስኃን የዴምህት ምክትል ሊቀ-መንበር አድርጎ ይሾመዋል ። የማነ ድምፁ ጥቂት ጊዜ ከሻእቢያ ጋር የነሱ ተባባሪ መስሎ ከቆየና እምነታቸውን ካረጋገጠ በኋላ ፤ የዴምህትን ተዋጊዎች ይዞ በአዝማችነት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ በሻእቢያ ይታዘዛል ። ከ50 በላይ የሚሆኑ ተዋጊዎቹን አዘጋጅቶም የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ለውጊያ ይገባል ።ተዋጊዎቹ ራሳቸው በሻእቢያ የጭቆና ቀንበር የተሰቃዩ ስለነበሩ ፤ የነሱንም ህሳብ አስለውጦ ወደ 50 የሚጠጉትን ይዞ እጃቸውን ለወያኔ እንዲሰጡ ያደርጋል ። የየማነ ድምፁ የዴምህት መሪነትና ከሻእቢያ ጋር የነበረው ታሪክ በዚህ አይነት ይደመደማል ። ምክትሉ የነበረው ፍስኃ ኃይለ ምርያምም የዴምህት መሪ ይሆናል ።

ወደ ፍስኃ ኃ/ማርያም ጉዳይ ከመምጣቴ በፊት ስለ አንድ የሻእቢያ የስለላ ሰው ልንገራችሁ ። መቶ አለቃ ብርሃኔ ይባላል ። በደርግ ጊዜ ሻእቢያን የተቀላቀለ ሰው ነው ። ብርሐኔ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በፊት (በወያኔና በሻእቢያ የፍቅር ዘመን) በሐረርጌ በተለይ በጅጅጋና አካባቢዋ የሻእቢያ የስለላ መኮንን ሆኖ እንዲሰራ ተመድቦ ነበር ።

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እንደተጀመረ ወያኔ በመጀመሪያ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው የሻእቢያ ቋሚ ወታደራዊ ሰላዮች ውስጥ አንዱ መቶ አለቃ ብርሐኔ ነበር ። ብርሐኔ ወደ ኤርትራ ከተመለሰ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በተቋቋመ በአመቱ ለግንባሩ ወታደራዊ ስልጠና ለመስጠት ተመደበ ። መጠሪያ ስሙ ወታደራዊ አሰልጣኝ ይባል እንጂ ዋናው ስራው የአርበኞች ግንባርን ተዋጊዎች መሰለል ነው ። በዚህ ስራ ላይ እንዳለ በሻእቢያ እየተጠራ ወደ ሌላ ቦታዎች እየተወሰደ ለወራት ይቆይ ነበር ።

በኋላ ላይ በራሱ አንደበት ሲነገር እንደተሰማው መቶ አለቃ ብርሃኔ ከአርበኞች ማሰልጠኛ ጣቢያ የጠፋባቸው ወራት ፤ በሻእቢያ ወደሶማሊያ ተልኮ የነበረባቸው ወራት ነበሩ ። በሶማሊያ ቆይታው አንዳንዶች አልሻባብን እያሰለጠነ ነበር ሲሉ ፤ ሌሎች ደግሞ የለም የኦጋዴንን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባርን ተዋጊዎች (ኦብንግን) ሰራዊት እያሰለጠነ ነበር ብለውታል ። ያም ሆነ ይህ ብርሐኔ ወደሶማሊያ ሄዶ ወታደራዊ ስራ ሲሰራ የቆየ ሰው ነው ። ታዲያ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በፊት ጅጅጋ ወስጥ ለሻእቢያ የስለላ ስራ ይሰራ ስለነበር ፤ በሶማሊያ ተልእኮው ከኦብነግ ጋር በመቆየት ስልጠና ሰጥቷል የሚለው ሀሳብ የበለጠ ስሜት የሚሰጥ ይሆናል ። ከሶማሊያ እንደተመለሰ እንደገና ወደአርበኞች ግንባር አሰልጣኝነትና ሰላይነት ተመድቧል ።

ሌላውና የዛሬው ፅሁፌ አቢይ ግለሰብ ፤ ፍስኃ ኃ/ማርያም ተድላ ይባላል። የተንቤን ተወላጅ ነው ። በወያኔ የትግል ዘመን እሱም ታጋይ ነበር ። ወያኔ ጠቅላላ ኢትዮጵያን ከመቆጣጠሩ አስቀድሞ በወያኔ ሰራዊት ውስጥ የወታደራዊ ስለላ ስራ ሰርቷል ። በክንፈ ገ/መድህን የደሕንነት አስተዳደር ዘመን አዲስ አበባ ውስጥ ዘመናዊ የሰላይነት ስልጠና ከተሰጣቸው የመጀመሪያዎቹ የትግራይ ሰዎች አንዱ ሆኗል ። ፍስኃ ኃ/ማርያም ከዚህ ስለጠና በኋላ ለሶስት አመታት በአዲስ አበባ የደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ ለወያኔ አገልግሏል ።

በተለይ በፕሮፌሰር አስራት ወ/የስ የመላው አማራ ድርጅት ዙሪያ ይደረግ የነበረውን ስራ ከመሩት ሰዎች አንዱ የነበረ መሆኑን በራሱ አንደበት ይናገረው የነበር ታሪክ ነው ። በግልፅ በይናገረውም ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ ወያኔዎች መሃል በተፈጠረው ክፍፍል ምክንያት ወደ ኤርትራ እንደገባ ይገመታል ። ፍስኃ በዴምሕት ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን ያለው ፈላጭ ቆራጭ ሰው ነበር። ፍስኃ ኃ/ማርያም ከአርበኞች ግንባር መሪዎች ይልቅ በሻእቢያ ከፍተኛ አመኔታ የሚጣልበትም ሰው ነበር ። እስከ 2008 ዓ.ም. እ.ኤ.አ ድረስ ሻእቢያና ፍስኃ ዘይትና ሞተር ሆነው ተስማምተው ይሰሩ ነበር ።

በ2008 በኋላ ግን አለመግባባቶች ተፈጠሩ ። በተለይ ሻእቢያ ይዞት የመጣው አጀንዳ ለፍስኃ ኃ/ማርያም የሚዋጥለት አልሆነም። ለዴምሕት TPDM ተተኪ ወታደር ማግኘት ቀላል ስላልሆነ ፤ የሻእቢያ ወታደራዊ ምልምሎች ከዴምህት TPDM ጋር ይቀላቀሉና ይሰልጥኑ የሚል ሃሳብ ሻእቢያ ይዞ ብቅ ይላል ። ከዚያ በፊት ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይ (ዴምሕት) TPDM ውስጥ የሻእቢያ ምልምል ወታደሮች ፈፅሞ አልነበሩም ። በቀደመው ፅሁፌ እንደገለፅኩት ፤ ሻእቢያዎች በዚህ አዲሱ እቅዳቸው ዴምህትን TPDM የትሮይ ፈረስ ለማድረግ አስበዋል ። ፍስሃ ኃ/ማርያም የሻእቢያን የወደፊት እቅድ በአግባቡ ይረዳው አይረዳው መናገር አልችልም ። ሆኖም ግን በእርግጠኝነት መናገር የምችለው አንድ ጉዳይ አለ ።

ፍስኃን ለብቻየ በግል ላነጋግረው ብዙ ጥረት አድርጌአለሁ ። በጊዜው በአስመራ ውስጥ የማደርገውን እንቅስቃሴ ሁሉ እንደጥላ እየተከተሉ ያስቸግሩኝ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ ። የምናገረውን ሁሉ ካፌ እየወሰዱ ለሻእቢያ እንደሚያቀርቡም አውቅ ነበር ። ከፍስኃ ጋር በግልፅ ቀጠሮ በያዝኩባቸው ቦታዎች ሁሉ ተከታይ ጥላዎቼ ሳልፈልጋቸው ስለሚገኙ ፤ ቁም ነገር ልናወራ የምንችልባቸው ብዙ እድሎች አምልጠውኛል ። በሁኔታው መቸገሬ ስለገባው ይመስለኛል ፤ ራሱ አመቻችቶ ከሚከተሉኝ ጥላዎቼ ሰውሮ ሁለት ጊዜ ተገናኝተን ተነጋግረናል ። ውይይቶቻችን ያተኮሩባቸው ጉዳዮች ዴምሕትና TPDM የኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄ ? የዴምህት ባንዲራ አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ሆኖ ሳለ ለምን የአክሱም ሃውልት መሃከሉ ላይ ተደረገበት ? ሰዎች እየታፈሱ በግዴታ እንዲቀላቀሏችሁ ይደረጋል ይባላል ለምን ? በፕሮፌሰር አስራትና በመላው አማራ ላይ የተደረጉ አፈናዎች ላይ ስለነበረው ሚና ? የዘር ፖለቲካ በወደፊቲቱ ኢትዮጵያ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ችግርና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ተወያይተናል ። ከነዚህ ንግግሮቻችን እንደተረዳሁት ፍስኃ ኃ/ማርያም አገር ወዳድ ሰው ሆኖ አግኝቼዋለሁ ። የኢትዮጵያ የወደፊት እጣም እንደሚያሳስበው ተረድቼአለሁ ።

ከላይ የጠቀስኳቸው ከሱ ጋር ያነሳኋቸው ነጥቦች የዛሬ ርእሶቼ ስላልሆኑ ካስፈለገ ሌላ ጊዜ የምመጣባቸው ይሆናሉ ። ሆኖም ግን አቢዩ ጉዳይ ከፍስኃ ጋር ያደረኳቸው ውይይቶችና ከዛም አልፎ ባደረገልን ግብዣዎች ላይ እንዳስተዋልኩት ስልጣኑን በፈለገው መንገድ ያለገደብ የሚጠቀም ሰው መሆኑን ተረድቻለሁ ። በአንድ አጋጣሚ እኔም ሆንኩኝ ሌሎች ከአሜሪካና ከአውሮጳ የሄድን ሰዎች በዴምሕት TPDM የምስረታ በዓል ላይ ተገኝተን ነበር ። በበአሉ ዋዜማ ላይ ፤አንዲት በሙያዋ ነርስ የሆነች ሴት አባልን ጨምሮ ፤የተወሰኑ የዴምሕት TPDM አባላትን የወያኔ ሰላዮች ናችሁ በሚል ፤ ጉድጓድ ውስጥ አስሯቸው አድሯል ።

የመጀመሪያው ፅሁፌ ላይ ፤ “ሻለቃ ዳዊት የዴምህት TPDM ተዋጊዎች ጋር አብሮ የሚኖር የእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸውን ተቆጣጣሪና በተዋጊዎቹ ላይ ያለገደብ ሙሉ ስልጣን ያለው ። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከሻለቃ ሐድጎ መባረር በኋላ የአርበኞች ግንቦት 7ና የድምህት ተዋጊዎች ላይ ሙሉ ስልጣን ያለው” ። ብዬ ገልጨው የነበረውን ሰው ታስታውሳላችሁ ። በሌላ አጋጣሚም ታውቁታላችሁና ላስታውሳችሁ ። በኢሳት ሚዲያ ላይ የጋዜጠኛውን እግር ጎንበስ ብሎ ለማጠብ የክርስቶስን ሰብዕና እንዲላበስ ስለተደረገው ሰው ትዝ ሳይላችሁ አይቀርም ። ከላይ የገለፅኳቸው የሁለቱም ሴናሪዮ ባለቤት አንድ ሰው ነው ። ሻለቃ ዳዊት ።

የዛሬዋ የሻለቃ ዳዊት ባለቤት የሆነችው ወጣት ከትግራይ በአፈሳ የመጣች ናት ። ይህች ልጅ ያለፈቃዷ በፍስኃ ኃ/ማርያም ለሻለቃ ዳዊት በሚስትነት በስጦታ ፤ አዎ በስጦታ እንደ እቃ የተሰጠች ልጅ ናት ። ሻለቃው ወደዳት ለፍስኃ መውደዱን ገለፀለት ፤ ፍስኃም አውጥቶ ሰጣት ። ዛሬ ያለውዴታዋ ከሻለቃው ሁለት ወልዳ ልጆች እያሳደገች ያለች ሴት ናት ። እስቲ ተመልከቱት ! የሰውን ልጅ ያህል ፍጡር እንደእቃ አውጥቶ በስጦታ መስጠት ። በነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ፍስኃ ኃ/ማርያም የአምባ-ገነንነት ባህርይ ያለው ሰው ነው ።

ስልጣኑንም ከምንም በላይ የሚወድ ሰው መሆኑን ታዝቤአለሁ ። ከላይ እንዳልኩት በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ፤ አዲሱ የሻእቢያ እቅድ ማለትም የሻእቢያ ተመልማዮችን ከዴምህት ተዋጊዎች ጋር እያዛነቁ ማሰልጠን የራሱን ስልጣን የሚሸረሽር መሆኑን በሚገባ ተረድቶታል ። የሻእቢያ ብሄራዊ ውትድርና ሰልጣኞች ከዴምሕት ጋር ተቀላቀሉ ማለት በፍስኃ ኃ/ማርያም ስልጣን ላይ አደጋ አንዣበበ ማለት ነው ።

በጊዜው ከነበረበት ተፅዕኖ በላይ በቀረችው ስልጣን ውስጥ የሻእቢያ ሰላዮችና ወታደራዊ መኮንኖች ሊርመሰመሱበት ነው ። ፍስኃ ያልተገነዘበው አንድ ጉዳይ ነበር ። በዴምሕት ላይ የነበረውን ስልጣን የምር አድርጎ ወስዶት ነበር ። ሻእቢያ ደግሞ እሱን የሚያየው እንደ ባለሙሉ የዴምህት ባለስልጣን አድርጎ ሳይሆን እንደ አሻንጉሊቱ ነበር ። አሻንጉሊቱ የተሰጠውን ገፀ-ባህርይ በሚገባ እስካልተጫወተ ድረስ በሌሎች ተዋንያን ይተካል ። ስለዚህ የሻእቢያ ምልምል ወታደሮች ከዴምሕት ሰራዊት ጋር መቀላቀላቸውን ደጋግሞ ከነ-ኮረኔል ፍፁምና ሌሎች የሻእቢያ መኮንኖች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ላይ አጥብቆ ተቃውሟል ። በዚህም በራሱ ላይ የመጨረሻዋን የሞት ፍርድ አሻራ በሰም አተመ ።

ከመጨረሻዋ የስብሰባ ቀን ቀደም ብሎ በተደረገ ወታደራዊ ስብሰባ ላይ ከሻእቢያ በኩል ኮለኔል ፍፁም ፤ ሻለቃ ዳዊት ፤ ሻለቃ ኃድጉ ፤መቶአለቃ ብርሐኔ ( ከላይ የገለፅኩት ፤ ወደ ሶማሊያ ይላክ የነበረው ) እና ሌሎች ሁለት በመቶ-አለቃ ማእረግ ላይ የሚገኙ መኮንኖች በዴምሕት TPDM በኩል ደግሞ ራሱ ፍስኃ ሃ/ማርያም እንደሚገኙ ቀጠሮ ተሰጥቶ ነበር ስብሰባው የተበተነው ።

በመጨረሻይቱ ስብሰባ ላይ የተገኙት ግን ሁለት ሰዎች ብቻ ነበሩ ። ፍስኃ ኃ/ማርያምና መቶ-አለቃ ብርሃኔ ። ሌሎቹ የሻእቢያ መኮኖንች አንዳቸውም በስብሰባ ላይ አልተገኙም ። መቶአለቃ ብርሐኔ በዛች ቀን ለስብሰባ ሳይሆን በሻእቢያ ተልእኮ ተሰጥቶት የመጣ ሰው ነበር ። መኖሪያው አርበኞች ግንባር ማሰልጠኛ አካባቢ በመሆኑ ወደስብሰባው ከመሄዱ በፊት ከተለመደው ባህርይው ውጪ አንቀዥቅዦት እንደነበር በቦታው የነበሩ የአርበኞች ግንባር የአይን ምስክሮች ይናገራሉ ። እርሱ ይቆጣጠረው በነበረው የአርበኞች ግንባር ፅ/ቤት ውስጥም ወደ ስብሰባው ከመሄዱ በፊት የአንበሳ ስእል ስሎ ለመታሰቢያ ጥሎ መሄዱን አርበኞቹ ያስታውሳሉ ።

አንዳንዶች እንደሚገምቱት የግድያው ተልእኮ ለሱ በመሰጠቱ ደስተኛ አልነበረም ።ብርሐኔና ፍስኃ ወዳጆች ነበሩ ። አብረው ሰርተዋል ፤ በልተዋል ፤ ጠጥተዋል ። የሰው ልጅ የሌላውን ሰው ነፍስ ለመቀማት ምክንያት Motive ይፈልጋል ። ገንዘብ፤ ፍቅር ፤ ቅናት ፤ እና ሌሎችም ለግድያ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ ። በሁለቱ መካከል ግን በግል ምንም አይነት ጥላቻም ሆነ ለግድያ የሚያዳርስ ቂም አልነበረም ። የነበረው የሻእቢያ ትእዛዝ ብቻ ነው ። የሻእቢያ ወታደራዊ ትእዛዝ ነውና ያን አለመወጣት በራሱ ላይ የሚያመጣው አደጋ እስከ ህይወት ማጣት ሊያደርስ እንደሚችልም ጠንቅቆ ያውቃል መቶ-አለቃ ብርሐኔ ። ተልእኮውንም በዚያች የስብሰባዋ ስፍራ ላይ ማንም ተሰብሳቢ በሌለበት መወጣት ነበረበት ። ለሎቹ የሻእቢያ ተወካዮችም በስብሰባው ላይ ያልተገኙት ለዚህ ነበር ። ይህን ሲያስበው ሰው ነውና ፤ ምናልባት ከስሜቱ ጋር ሳይጋጭ አልቀረም ። በዚያች የስብሰባ ቦታ ላይ የተሰጠውን ተልእኮ ሳይወጣ ቀረ ።

ፍስኃ ኃ/ማርያምም ስብሰባው በሌላ ቀን ሊጠራ ይችላል ከሚል ህሳቤ ከስብሰባው ውጪ አቁሟት በነበረችው ፒክ-አፕ መኪናው ወደ ጉዳዩ ለመሄድ ተነሳ ። መቶ-አለቃ ብርሐኔም ራይድ ጉልች ድረስ እንዲሰጠው ፍስኃን ይጠይቀዋል ። በፍስኃ መኪና ጉልች እስከምትባለው ትንሽ ከተማ ድረስም አብረው ተጉዘዋል ። ጉልች ላይ መቶ-አለቃ ብርሐኔ ከመኪና እንዲያወርደው ፍስኃን ይጠይቀዋል ። አገር ሰላም ነው ብሎ መቶ-አለቃውን የተሰናበተው ፍስኃ ሳያስበው በሽጉጥ ጥይት ጭንቅላቱ ላይ ይመታል ። ገዳዩም የሻእቢያ የስለላ መኮንን ፤ ራይድ በፍስኃ የተሰጠው መቶ-አለቃ ብርሃኔ ነበር ።

መቶ አለቃ ብርሐኔን ሻእቢያ ከወሰደው በኋላ እስካሁን የት እንዳደረሰው ባይታወቅም ፤ በቀጣዮቹ ቀናት ግን መቶ አለቃው የአይምሮ ህመምተኛ ሆኗል የሚለው ወሬ በአርበኞቹና በዴምህት ተዋጊዎች መካከል ተነዛ ።

ከሻእቢያ ስትወዳጅ ፤ ፍርድ ሳታገኝ ፤ማንነትህ እንኳ ሳይታወቅ ፤ተዋግቶ ሞተ ተብለህ በጀግንነት ሳይዘመርልህ ወይም በዘመድ አዝምድ በወግ ሳይለቀስልህ የትም ድፍት ብለህ ትቀራለህ ። የፍስኃ ኃ/ማርያምን ደም የጉልች አሸዋማ ደረቅ መሬት ምጥጥ ሲያደርገው ደቂቃዎች አልወሰዱበትም ። ዛሬ በአሸዋማው መሬት ላይ የደሙ አሻራ እንኳ የለም ። ፍስኃ ኃ/ማርያምም ተረት ሆኖ ቀርቷል ። ሻእቢያን ስትጠጋ ደምህ ደመ-ከልብ ሆኖ ይቀራል ። ወዳጄ ፍስኃ ሆይ የማይታወቀውና ምልክት እንኳ የሌለው የተቀበርክበት አፈር ይቅለልህ !

የሁለተኛው የዴምሕት መሪ የፍስኃ ኃ/ማርያም የመጨረሻ እጣም እንዲህ ሆኖ አበቃ ። ተፈፀመ ።

ኦገስት 24 ቀን 2015 እ.ኤ.አ.
ላስ ቬጋስ ኒቫዳ ።

 

Posted  By-Lemlem Kebede

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s