ነጋዴዎች በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አሠራር መማረራቸውን ተናገሩ -‹‹ኔትወርክ የለምና ስብሰባ ላይ ናቸው አማሮናል›› ነጋዴዎች

ነጋዴዎች በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አሠራር መማረራቸውን  ተናገሩ 

የተነሱት የቅሬታ ነጥቦች በቀጣዩ ሩብ ዓመት ምላሽ ይሰጣቸዋል›› የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ከፍተኛ፣ መካከለኛና አነስተኛ ነጋዴዎች በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አሠራር እየተቸገሩና እየተማረሩ መሆኑን ጥቅምት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በጊዮን ሆቴል ከባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ጋር ለአንድ ቀን ባደረጉት የምክክር መድረክ ላይ ተናገሩ፡፡

የ2006 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምንና የ2007 በጀት ዓመትን ዕቅድ በሚመለከት በባለሥልጣኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ፣ የመድረኩ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት እንዳብራሩት፤ ለሚያቀርቧቸው ዕቃዎች ዋጋ ለመተመን የጉምሩክ ሲዲ (ዋጋ መተመኛ) እንደሚሻል የተነገራቸው ቢሆንም፣ ስምምነት ላይ ግን አልተደረሰም፡፡ ባለሥልጣኑ በሲዲ የዋጋ ተመን ከማውጣት ይልቅ፣ ሸቀጦቹ በሚገኙባቸው አገሮች ቢሮ ቢከፍትና ዋጋ እያጠና ቢያቀርብላቸው የተሻለ መሆኑን ታዳሚዎቹ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ኦዲተሮች ‹‹መመርያ ነው፣ ሕጉ ነው›› እያሉ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩባቸው መሆኑን የገለጹት ነጋዴዎቹ፣ ‹‹ሕጉ ካስቸገረ ለምን አይሻሻልም?›› በማለትም ጠይቀዋል፡፡ በኮንቴይነር የሚገባን ዕቃ የቀረጥ ሥርዓት ፈጽሞ ለማስለቀቅ ሲሄዱ ‹‹ሥልጠና ላይ ናቸው›› በሚል መልስ ረጅም ጊዜ ለመቆየት እንደሚገደዱ የተናገሩት ነጋዴዎቹ፣ ባለሥልጣኑ ትልቅ መሥሪያ ቤት ከመሆኑም በተጨማሪ የአገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ተቆጣጣሪ እንደመሆኑ መጠን፣ ተተኪ ሰው ሊያስቀምጥ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

‹‹ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ለመመካከር በሚል ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በርካታ ሮሮዎች ተነስተዋል፡፡ ‹‹ኢንቨስተሮችን ያስቸገረው ነገር የክሊራንስ ጉዳይ ነው፡፡ እንዴት ነው የሚፈታው?›› በማለት አስተያየት የሰጡ ነጋዴ እንደተናገሩት፣ የባለሥልጣኑ ኦፊሰሮች ክሊራንስን በሚመለከት አሠራራቸው እንደፈለጉና እንዳሻቸው ናቸው፡፡

በተለይ የተመላሽ ገንዘብ ጉዳይ የላኪዎችንና የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ካፒታል እየጐዳው መሆኑን የገለጹት ነጋዴዎቹ፣ ለነጋዴው በፍጥነት እንዲመለስለትም ጠይቀዋል፡፡

ከዋጋ በታች (Under Invoicing) ስለሚቀርብ ዕቃ ባለሥልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ ባለመሥራቱ ፍትሐዊ ያልሆነ ውድድር እንዲኖር እያደረገ መሆኑን የገለጹት ነጋዴዎቹ፣ የቁጥጥሩ ማነስ የአገር ውስጥ ነጋዴዎችን እየጐዳም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ብቃት አረጋጋጭ አካላትና ፈቃድ ዕድሳት ጋ ብዙ ችግሮች እንዳሉ የገለጹት ነጋዴዎቹ፣ ንግድ ሚኒስቴር ገቢዎች የሰጠውን ክሊራንስ እንደማይቀበልና በውጭ ኦዲተሮች እንዲያሠሩ እያስገደዳቸው መሆኑ ጠቁመው፣ ሁለቱም ተቋማት የሚሠሩት ለአገር በመሆኑ ለምን እንደማይነጋገሩ ግራ እንደገባቸው ገልጸዋል፡፡

በቁርጥ ግብር ስም የተፈለገውን ያህል ግብር እየተጫነባቸው መሆኑንና አሠራሩ ደግሞ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጠ መሆኑን የጠቆሙት ነጋዴዎቹ፣ የባለሥልጣኑ ከፍተኛ አመራሮች እታች ካለው ነጋዴ ጋር በመገናኘት እየደረሰበት ያለውን ችግር ላይም ለመወያየት ጠይቀዋል፡፡ በተለይ በየክፍለ ከተማው ያሉ የባለሥልጣኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ምሬታቸውን ከፍ እንዳደረጉት ጠቁመዋል፡፡

ነጋዴዎች በክልልም እንዳሉ በመናገር፣ ከግብር ጋር በተገናኘ ችግር ሲፈጸም ክስም ሆነ አቤቱታ የሚሰማው አዲስ አበባ ብቻ መሆኑ ተገቢ ባለመሆኑ፣ በክልልም ቢደረግ የተሻለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በግብር ዙሪያ ውሳኔ የሚሰጡ የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ‹‹እኔ ያልኩት ብቻ ትክክል ነው፤›› በማለት የማዳላት ሥራ እንደሚሠራ፣ ድንገተኛ ፍተሻ በማለት ፈታሾች አንዱን ከአንዱ ጋር በማቀላቀል ሥራ እያጓተቱ መሆኑንም ነጋዴዎቹ አስረድተዋል፡፡

በመመርያዎች መሠረት ሥራዎች እንደማይፈጸሙ አስተያየት ሰጭዎቹ ሲናገሩ፣ ጠቅለል ያለ አስተያየት ከመስጠት ይልቅ መነጋገር የተሻለ እንደሆነ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌ  ተናግረዋል፡፡

‹‹ኔትወርክ የለም፣ ሥልጠና ላይ ናቸው …›› የመሳሰሉትን ተልካሻ ምክንያቶች በመስጠት ሥራዎች እየተጓተቱባቸው በመሆኑ፣ መሥሪያ ቤቱ የአሠራር ሲስተሙን በማሻሻል ነጋዴውን በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲያገለግል እንዲደረግላቸው ነጋዴዎቹ ጠይቀዋል፡፡

የግብር አዋጁ አሥር ዓመታት ስላለፉት ቢሻሻል፣ በድሬዳዋ፣ በኮምቦልቻና በናዝሬት የሚቀረጡ የንግድ ዕቃዎች ላይ ትኩረት ቢሰጥ፣ በቦሌ የሚገቡ ዕቃዎች እኩል የማይቀረጡበት ሁኔታ ቢጠና የሚሉና ሌሎች በርካታ ችግሮችን አንስተዋል፡፡

የመጋዘን ኪራይ፣ መብራት የለም ማለት፣ ሲስተም አይሠራም ማለትና ሥልጠና ላይ ናቸው ማለት የተለመዱና አሳፋሪ ነገሮች በመሆናቸው ባለሥልጣኑ ሊያስብባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የተሻሻለው አዋጅም በፍጥነት እንዲተገበር አሳስበዋል፡፡

በነጋዴዎቹ ለተነሱት ጥያቄዎች የባለሥልጣኑ የተለያዩ ዘርፎች ምክትል ዳይሬክተሮች ችግሩ እንዳለ በማመን እንደሚስተካከል ገልጸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ለተነሱት ጥያቄዎችና ማስተካከያዎች በቀጣዩ ሩብ ዓመት ምላሽ ይሰጣቸዋል፤›› በማለት ለነጋዴዎቹ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ የሰጡት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌ ሲሆኑ፣ ‹‹ስብሰባ ይበዛል›› በሚል ለቀረበው አቤቱታ በሰጡት ምላሽ ‹‹ስንሰበሰብ ግብር ከፋዩን እንዴት እናስደስት? ኪራይ ሰብሳቢነትን እንዴት እናስወግድ? ፈጣን አገልግሎት በምን መልኩ እንስጥ?›› በማለት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በመሆኑ፣ ስብሰባ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ስብሰባን የሚያማርረው ነጋዴ ብቻ ሳይሆን የባለሥልጣኑ አንዳንድ ሠራተኛም፣ አሠራሩ እንዳይታይበት ስለሚፈራ እንደሚማረርም አክለዋል፡፡ በራሱ የሚተማመንና ብቃት ያለው ሠራተኛ ግን አጭር ስብሰባ በማድረግ፣ ራሱንና አሠራሩን ግልጽ በማድረግ ስለሚታወቅ፣ ለሚሰጠው ውሳኔ ኃላፊነት እንደተሰጠውና መወሰንም እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

እንደ ጸሐፊ የሚያገለግል ማለትም፣ በራሱ ስለማይተማመን ወደ ላይ አመራር የሚመላለስና ውሳኔ መስጠት የማይችል ሥራ አስኪያጅ እንዳለ በነጋዴዎቹ ለተነሳው ጥያቄ ‹‹የተጋነነ ነው፣ እኛ እንደዚህ ዓይነት ሥራ አስኪያጅ የለንም፤›› ብለዋል፡፡ አንዱ ከአንዱ ሊለያይ እንደሚችል፣ ብቃትና ጽናት ያላቸው ሊመሰገኑ የሚገቡ ሠራተኞች እንዳሉም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሥራው በጣም አድካሚ ቢሆንም ይኸንን ተቋቁመው በአግባቡ የሚሠሩ ስላሉ፣ ግብር ከፋዩ ሊያስመሰግናቸውና ዕውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባም አክለዋል፡፡ አሳፋሪ በሆነ ሁኔታም ሥነ ምግባር ያላቸው ሠራተኞች እንዳሉም አቶ በከር አልሸሸጉም፡፡ የማይገባ ጥቅም የሚጠይቁ ሠራተኞች መኖራቸውን ጠቁመው ሕዝቡ ‹‹እከሌ›› ብሎ እንዲያጋልጥም አሳስበዋል፡፡

‹‹ኔትወርክ የለም›› የሚለው ችግር የቴሌ ብቻ ሳይሆን የባለሥልጣኑ የአይቲ ችግርም በተወሰነ መልኩ እንዳለ ገልጸው፣ ሰው ሰራሽ የሆነ ችግርም መኖሩን በመጠቆም ለማስወገድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአገር ውስጥ ታክስ ገቢ አሰባሰብ አዋጅ ዙሪያ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን የገለጹት አቶ በከር፣ የተሻሻለው አዋጅም በነጋሪት ጋዜጣ እንደወጣ ተፈጻሚ ስለሚሆን በትዕግሥት እንዲጠብቁ ተናግረዋል፡፡

የዋጋ ትመናና ከዋጋ በታች ስለሚገቡ ዕቃዎችና ሌሎች በተነሱት ጉዳዮች ላይ ባለሥልጣኑም ዝም አለማለቱን አቶ በከር ገልጸዋል፡፡ አቶ በከር ዘርዘር ያለ ምላሽ ሰጥተው የምክክር መድረኩ ተጠናቋል፡፡

Posted By-Lemlem Kebede

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s