የህግ ባለሙያዎችን ያከራከረው የጋዜጠኛ ተመስገን ክስ

የህግ ባለሙያዎችን ያከራከረው  የጋዜጠኛ ተመስገን ክስ

የቀድሞ የ“ፍትህ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ በተከሰሰበት የወንጀል ክስ ጥፋተኛ ተብሎ የ3 ዓመት እስርና የ10ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ መወሰኑ የህግ ባለሙያዎችን ጨምሮ ብዙዎችን ያነጋገረ ርዕሰጉዳይ ሆኗል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ጋዜጠኛ ተመስገን የ“ፍትህ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሲሰራ፣ በጋዜጣው ላይ የሚወጡ ፅሁፎችን የመቆጣጠር ኃላፊነት እያለበት አመፅ ቀስቃሽ፣ የመንግስትን ስም የሚያጠፉና የህዝቡን ስሜት የሚያናውጡ ፅሁፎችን አትሞ በማውጣቱ ክስ እንደተመሰረተበት ይታወሳል፡፡
አቃቤ ህግ እነዚህን ክሶች ሲያቀርብ፣ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፆች መሰረት አድርጎ ሲሆን የወንጀል ህጉን 257(ሀ)ን በመተላለፍ፣ አመፅ ቀስቃሽ የሆኑ ፅሁፎችን በጋዜጣው እንዲታተሙ በማድረግ፣ የወንጀል ህግ 244ን በመተላለፍ የመንግስትን ስም የሚያጠፉና በሃሰት የሚወነጅሉ ፅሁፎችን እንዲታተሙ በማድረጉና የወንጀል ህጉን አንቀፅ 486 (ሀ)ን በመተላለፍ፣ የህዝብ ስሜትን የሚያናውጡ ፅሁፎች እንዲታተሙ ማድረጉን ጠቅሶ ነው፡፡
የ3 ዓመቱ እስራትና የ10ሺ ብር መቀጮውም እነዚህን አንቀፆች በተለይም የወንጀለኛ መቅጫ አንቀፅ 257ን (መንግስትን በአመፅ ለመጣል ግዙፍ ያልሆነ መሰናዳትን በተመለከተ የሚደነግግ ነው) መሰረት በማድረግ የተላለፈ ነው፡፡
በሌላ በኩል የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነትን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 590/2002/፤ በመገናኛ ብዙሃን ሊፈፀሙ የሚችሉ የህግ ጥሰቶችን በየአንቀፆቹ ከዘረዘረ በኋላ “ቅጣት” ብሎ የገንዘብ መቀጮን ብቻ ያስቀምጣል፡፡ በእስራት ስለሚፈፀም ቅጣት አዋጁ ያስቀመጠው ድንጋጌ የለም፡፡
በአዋጁ ክፍል አምስት፤ “ህጋዊ እርምጃዎችን ስለመውሰድ” በሚለው ርዕስ ስር፣ በአንቀፅ 45 ስለ ቅጣት እንዲህ ሲል ይደነግጋል፡- “በዚህ አዋጅ የተደነገገውን የተላለፈ ማንኛውም ሰው ከብር 20 ሺ እስከ ብር 200 ሺ ባላነሰ መቀጮ ይቀጣል”፡፡
ሰሞኑን በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ መሰረት እስራትና ቅጣት መወሰኑን ተከትሎ የተለያዩ የህግ ባለሙያዎችና አስተያየት ሰጪዎች፤ “ጋዜጠኛው የገንዘብ መቀጮን ብቻ የሚደነግገው የፕሬስ አዋጁ እያለ በወንጀለኛ መቅጫ አንቀፆች መከሰሱ አግባብ አልነበረም” ብለዋል፡፡
እነዚህ ወገኖች፤ የመገናኛ ብዙሃንን የመረጃ ነፃነትን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ አንቀፅ 49 ከአዋጁ ጋር ስለሚቃረኑ ህጎች እንዲሁም በአንቀፅ 50 ላይ ስለተሻሩ ህጎች የተጠቀሱትን አንቀፆች ዋቢ በማድረግ መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡
በአዋጁ አንቀፅ 49 ላይ፤ “ከዚህ አዋጅ (በ2002 የወጣው የፕሬስ አዋጅ ማለቱ ነው) ጋር የሚቃረን ማንኛውም ህግ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ ትዕዛዝ ወይም የተለመደ አሰራር በዚህ አዋጅ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚ አይሆንም” ይላል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ት/ቤት መምህር፤ በ1996 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንዳንድ አንቀፆች እንደገና መታየት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ በተለይም ተመስገን ላይ ለክስ መነሻ የሆኑት የወንጀለኛ መቅጫ አንቀፆች ከህገመንግስቱ አንቀፅ 29፣ ሃሳብን በነፃነት ከመግለጽ ጋር እንዲጣጣሙ ተደርገው መቀረፅ ነበረባቸው ይላሉ፡፡
“አንድ መንግስት በሚሰራቸው ስህተቶች በሚገባ ተብጠልጥሎ ካልተተቸ ዲሞክራሲያዊ የሚያስብለውን መሰረት ያጣል” የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ በህጎቹ ላይ አመፅ መቀስቀስ፣ የመንግስትን ስም ማጥፋትና አመኔታ ማሳጣት የሚሉት አንቀፆች ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ መብት አንፃር በጥንቃቄ መታየትና መታረም እንዳለባቸው ይገልፃሉ፡፡ “የፕሬስ አዋጅ ተብሎ በህግ መቀመጡን ራሱ እቃወማለሁ” ያሉት የህግ መምህሩ፤ “የፕሬስ አዋጁ ስለ መረጃ አጠያየቅና አሰጣጥ፣ ክልከላ ስለሚደረግባቸው እንዲሁም ከስም ማጥፋት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንዴት ሊታዩ ይችላል ከሚለው ሃሳብ ውጪ አሁን ጋዜጠኛ ተመስገን ከተከሰሰባቸው ጉዳዮች ጋር ግንኙነት ያላቸው አንቀፆች በሚገባ የሉትም” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ተመስገን በየትኛው ህግ አንቀፆች መጠየቅ ነበረበት በሚለው ላይ አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ ብለዋል – መምህሩ፡፡
የህግ አማካሪና ጠበቃ ተማም አባቡልጋ በዚህ ጉዳይ ላይ መደናገር የተፈጠረው ለምን እንደሆነ ሲያስረዱ፤ “ከወንጀለኛ መቅጫ ህጉ በተጨማሪ የፀረ-ሽብር አዋጅና የፕሬስ አዋጅ በስራ ላይ እንዲውሉ በመደረጉ ነው” ይላሉ፡፡ አንድ አገር ውስጥ የተለያዩ የወንጀል ህጎች መኖራቸው ለግለሰብ ብቻ ሳይሆን ለህግ ባለሙያውም አደናጋሪ መሆኑን ጠቁመው፤ በሃገሪቱ አንድ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ብቻ መኖር ነበረበት ብለዋል፡፡ “አሁን አቃቤ ህግ፤ ጋዜጠኛን መክሰስ ሲፈልግ ሲያሻው በፀረ-ሽብር ህጉ አሊያም በወንጀል ህጉ፣ ደስ ካለውም በፕሬስ ህጉ ሊከስ እንዲችል ተመቻችቶለታል” ባይ ናቸው፡፡
መጀመሪያ የወንጀለኛ ህጉ፣ ቀጥሎ የፕሬስ አዋጁ እንደ መውጣቱና  የተፈጻሚነት ወሰንን የሚደነግግ እንደመሆኑ ፕሬስን የተመለከቱ ጉዳዮች ተፈፃሚ መሆን የሚገባቸው በ2002 በወጣው የፕሬስ አዋጁ ነው ያሉት ጠበቃው፤ የተመስገን ጉዳይም በዚህ መሰረት መታየት ነበረበት ብለዋል፡፡
የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን በበኩላቸው፤ ከሚዲያና ብሮድካስት ጋር የተያያዘ ወንጀል በሁለት መንገድ ነው የሚታየው ይላሉ፡፡ የሚዲያውን ተቋማት አሰራር ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ በመጣስ የሚሰራ ጥፋትን ተከትሎ የሚጣል ቅጣት አለ የሚሉት አቶ አምሃ፤ ይህ መሰሉ በመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነፃነት አዋጅ የሚዳኝ እንደሚሆን ይገልፃሉ፡፡ በወንጀል  መቅጫ ህጉ ላይ የተደነገጉትን መጣስ ደግሞ ሌላኛው ወንጀል እንደሆነ ጠበቃው ያስረዳሉ፡፡
የወንጀል ህጉ በእርግጥም ሃሳብን በነጻነት ከመግለፅ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ያስነሳል ያሉት አቶ አምሃ፤ ነገር ግን ጋዜጣን እንደ መሳርያ ተጠቅሞ በወንጀል ህጉ ላይ የተደነገጉትን መጣስ የሚታየው በወንጀል ህጉ ነው ይላሉ፡፡
“ተመስገን ከተከሰሰባቸው ሶስቱ አንቀፆች መካከል ጥፋተኛ ተብሎ ቅጣት የተጣለበት አንቀፅ 257፣ የሚዲያ ውጤቶችን በመጠቀም ህዝብን ለአመፅ መቀስቀስ ወንጀል ነው ሲል ቅጣቱንም አያይዞ ይደነግጋል፤ ይሄ ህገ መንግስታዊ ነው አይደለም የሚለው በራሱ የሚያነጋግር ነው” ያሉት ጠበቃው፤ የአመፅ መቀስቀስ የመሳሰሉትን የሚከለክለው አንቀፅ ያለው የወንጀል ህጉ ላይ ነው እንጂ የመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ላይ አይደለም ብለዋል፡፡ የመንግስትን ስም ማጥፋትና በሃሰት መወንጀል የሚለውም በወንጀል ህጉ ላይ እንጂ በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ላይ እንደሌለ፤ የህግ ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡
በጥቅሉ የመገናኛ ብዙሃን አዋጁ በራሱ በተቋሙ የሚጣሱ ደንቦችንና መመሪያዎችን የሚመለከት ነው ያሉት ባለሙያው፤ የተመስገን በወንጀል ህጉ መከሰሱ ብዙም አጠያያቂ አይሆንም ብለዋል፡፡
ተመሳሳይ ክሶችን ከሚያደራጁ አቃቢያን ህግ መካከል ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ አቃቤ ህግ  በሰጡት አስተያየት፤ የተመስገን ጉዳይ እያከራከረ መሆኑን እንደተገነዘቡ ጠቅሰው የመገናኛ ብዙሃን ህጉ የወንጀል ህጎቹን አንቀፅ ያልሻራቸው በመሆኑ፣ በዚሁ አግባብ ክሱ እንደተደራጀና አቃቤ ህግን በወንጀል ከመክሰስ የሚያግደው የህግ ድንጋጌ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
የፕሬስ አዋጅ፣ የፀረ-ሽብር አዋጅ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ እና በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 ሃሳብን በነፃነት ስለመግለፅ የተደነገጉት አንቀፆች ዛሬም የህግ ባለሙያዎችን ሳይቀር ማከራከራቸውን ቀጥለዋል፡፡

Source-addisadmas.com

Posted By-Lemlem Kebede

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s