የሦስቱ ጀነራሎች ዕጣ ፈንታ

ነፃ አስተያየት

በኢትዮጵያ ታሪክ ዘመናዊና መደበኛ ሠራዊት የተመሰረተው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን በ1927 ዓ.ም ነው፡፡ ይህ ሠራዊት ከጦር ሜዳ ውሎ ባሻገር ፖለቲካን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ በሆኑ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ተሳትፎ ነበረው፡፡
የፖለቲካውን ተሳትፎ እንኳን በስሱ ብንመለከተው፣ ከ1966 እስከ 1985 በነበሩት ዓመታት የኢትዮጵያን አምስት ያገር መሪዎች አፍርቷል፡፡ አራቱ በደርግ ዘመን ርዕሰ ብሔሮች ሆነው ሲያገለግሉ፣ አንዱ ደግሞ የኢህአዴግ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡
በደርግ ዘመን አገሪቱን የመሩት ጀነራል አማን አንዶም፣ ጀነራል ተፈሪ በንቲ፣ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምና ጀነራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ናቸው። የኢህአዴጉ ፕሬዚዳንት ደግሞ መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ስለ ጦሩ አመሠራረትና ሂደት ከሚመጣው ሳምንት ጀምሮ በዝርዝር እንመለከተዋለን። ለዛሬ ግን የቆምሻ ያህል ስለ ሦስት ጀነራሎች እጣ ፈንታ እንመለከታለን፡፡
ሦስቱ ጀነራሎች ማለትም ጀነራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ጀነራል ከበደ ገብሬ እና ጀነራል መንግስቱ ነዋይ፤ ጦሩ ሲመሰረት በአፍላ ዕድሜያቸው ተመልምለው በመኮንነት ማዕረግ ለመመረቅ ሆለታ ከከተቱት ወጣቶች መሃል ናቸው፡፡ የጣልያን ወረራ አይቀሬነትን የተገነዘቡት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፤ ከስዊዲን አገር አምስት የጦር መኮንኖች በማስመጣት፣ በ1927 ዓ.ም የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤትን አቋቋሙ፡፡ ስልጠናው ሳይጠናቀቅ የፋሽት ኢጣልያ ወረራ በመጀመሩ ሰልጣኞቹ ለግዳጅ ተጠሩ፡፡
ሰልጣኞቹ እንደ አንድ የተደራጀ ጦር ሆነው መዋጋት ስለነበረባቸው በትምህርት ቤቱ ቆይታቸው ባሳዩት የቀለም ትምህርት እና ወታደራዊ ቅልጥፍና፣ የአመራር ክህሎታቸው እየታየ ሹመት ተሰጣቸው። በዚህ የተነሳም ሙሉጌታ ቡሊና ከበደ ገብሬ የሻለቃ ማዕረግ፣ መንግስቱ ነዋይ ደግሞ የመቶ አለቃ ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡
ሦስቱም ጀነራሎች ከሌሎቹ የጦር ጓዶቻቸው ጋር በመሆን የፋሽስት ኢጣልያን ወረራ ለመመከት ዝግጁ ሆኑ። ጦሩ የተሰጠው የጦር ግዳጅ ጣርማ በር ላይ በመመሸግ ወራሪውን ኃይል መመከት ነበር፡፡ ሆኖም በታጠቀው የጦር መሳሪያ ብልጫ እና የሠራዊት ብዛት የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር በቀላሉ ድል አደረጋቸው። ኢትዮጵያ ለጊዜውም ቢሆን በኢጣልያ ቁጥጥር ስር ዋለች፡፡ በዚህ ጊዜ ጦሩ በአንድ ላይ ሆኖ ትግሉን መቀጠል አልቻለም። ከፊሉ ጥቁር አንበሳ የሚል ድርጅት በመመስረት ትግሉን ለመቀጠል ወደ ምዕራብ ሲያቀና፣ ሌሎች በሄዱበት አካባቢ ካገኙአቸው  አርበኞች ጋር ሲቀላቀሉ፣ የተቀሩት ፋሽስት ኢጣልያ የጦሩን አባላት እያደነ መግደል ሲጀምር ወደ ስደት አቀኑ፡፡
ወደ ስደት ካቀኑት መሃል ጀነራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ጀነራል ከበደ ገብሬ እና ጀነራል መንግስቱ ነዋይ ይገኙበታል፡፡ ሦስቱም ጀነራሎች የተሰደዱት ወደ ጅቡቲ ነው፡፡ ጅቡቲ ውስጥ ሦስቱም ከሌሎች ስደተኛ የጦር ጓዶቻቸው ጋር በመሆን ክፉውንም ደጉንም አብረው አሳልፈዋል፡፡ በወቅቱ ከሦስቱም ጋር ጅቡቲ ከነበሩት መሃል በወቅቱ አቶ ኋላ ላይ ጀነራል ወልደሥላሴ በረካና ጀነራል ወልደዮሐንስ ሽታ ይገኙበታል፡፡ ጅቡቲ ውስጥ ካጋጠማቸው አስከፊ የስደት ኑሮ በላይ ያንገበግባቸው የነበረው በፋሽስት ኢጣልያ ለተወረረችው አገራቸው በሞያቸው ማገልገል አለመቻላቸው ነበር፡፡ አረረም መረረም የጅቡቲ የስደት ኑሮዋቸውን በአንፃራዊ ሰላም ለተወሰኑ ዓመታት ሲመሩ ቆይተው፣ ፈረንሳይ በናዚዋ ጀርመን ድል ተመታ ስትያዝ፣ ኢጣልያ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የሆነችውን ጅቡቲን በአየር ኃይሏ መደብደብ ጀመረች፡፡
በዚህ ወቅት ጅቡቲ ውስጥ መቆየቱ ለአደጋ መጋለጥ መሆኑን የተገነዘቡት ጀነራሎች ወደ ሌላ ቦታ መሄድ እንዳለባቸው ወሰኑ፡፡ በቅርብ ርቀት ወደምትገኘው የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት አካል ወደሆነችው በርበራ ማቅናት እንዳለባቸው ተስማሙ፡፡ በጅቡቲ የነበሩት የጦር ጓዶቻቸውን ብቻ ሳይሆን በወደቡ ይኖሩ የነበሩ ሴትና ህፃናት የሚገኙባቸው ኢትዮጵያውያንን በመያዝ ወደተባለው ቦታ በጀልባ ጉዟቸውን ጀመሩ፡፡
ጀልባዋን ከአንድ ህንዳዊ በመከራየት በህንዱ መሪነት ነው ወደ በርበራ ያቀኑት። እንቅስቃሴአቸውን ሁሉ በንቃት ሲከታተል የነበረው የኢጣልያ ስለላ መረብ በአካባቢው ለነበረው ጦሩ ስለጠቆመ፣ ከፍተኛ አደጋ ለማድረስ የሚችለውን ሁሉ አድርጐ አልተሳካለትም፡፡
ስደተኞቹ በርበራ እንደደረሱ እንደነሱው ሁሉ በርበራ ውስጥ በስደት ከሚኖሩ የጦር ጓዶቻቸው ጋር ተገናኙ፡፡ ከስደተኞቹ መሃል ጀነራል አሰፋ አየነ ኋላ ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባት እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት ይገኙበታል፡፡
በርበራም ከኢጣልያ ጥቃት አልተረፈችም። በዚህ ጊዜ የእንግሊዝ ጦር በባህር ኃይሉ ጭኖ ወደ የመን ዋና ከተማ ወሰዳቸው፡፡ ኤደን ለትንሽ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ኬንያ በመሄድ፣ ከሌሎች ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን፣ ጠላታችንን መዋጋት እንፈልጋለን በማለት ለእንግሊዞቹ ማመልከቻ ስለፃፉ እንግሊዞች ወደ ኬንያ ላኩአቸው፡፡
ልብሳቸውን አወለቁ፡፡ መሬት ላይ በመተኛት በጅራፍ እንዲገረፉ በቦታው የነበረው እንግሊዛዊ ለበታቾቹ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ በዚህ ጊዜ ስደተኞቹ በሙሉ ልብሳቸውን በማውለቅ ከጄነራል ከበደ ጎን ተኙ። በሁኔታው የተናደዱት እንግሊዞች ጫካ እንዲመነጥሩ ያዘዙአቸው ይሄኔ ነበር፡፡ ያ ሁሉ ግፍ ተፈፅሞባቸው፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አገራቸውን ከፋሽሽት ኢጣልያ ነፃ ለማውጣት ሱዳን መግባታቸው ተሰማ፡፡ ስደተኞቹ “ከንጉሠ ነገስታችን ጋር በመሆን አገራችንን ነፃ እንድናወጣ ወደ ሱዳን እንድንሄድ ፈቃድ ይሰጠን” በማለት አመለከቱ፡፡ እንግሊዞች ግን ጆሮ ዳባ ልበስ አሉ። በእንግሊዝ እርዳታ ሱዳን የገቡት ጃንሆይ፤ “ኬንያ ያሉት ስደተኞች ለማቋቁመው ጦር ስለሚስፈልጉኝ ይላኩልኝ” ብለው ስለጠየቁ፣ ኬንያ ያሉት እንግሊዞች ምንም ማድረግ አልቻሉም፡፡ ሆኖም በጀነራል ሙሉጌታ ቡሊና በጄነራል ከበደ ገብሬ ፅናትና ድፍረት የበገኑት እንግሊዞች፤ ሰበቦች በመደርደር ላለመልቀቅ ጣሩ፡፡ በዚህ የተነሳም ሌሎቹ እነሱን ትተን አንሄድም ብለው ስለቆረጡ ሁለቱንም ለመልቀቅ ተገደዱ፡፡
በኬንያ የከፋ ኑሮ ጫካ ሲመነጥሩ በነበሩበት ጉዜ በያዛቸው ወባ የተጎሳቆሉት ስደተኞች፤ ወደ ኡጋንዳ በመኪና ተጭነው ከሄዱ በኋላ በባቡር ወደ ሱዳን ተጓዙ። ሱዳን አገር ላይ ሶባ በተባለ ቦታ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ባቋቋሙት ጊዜያዊ ጦር ትምህርት ቤት በመግባት የተማሩትን የጦር ትምህርት ከለሱ፡፡
ከስልጠናው በኋላ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በመከተል አዲስ አበባ ገቡ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በጃንሆይ መሪነት እንደ አዲስ ተደራጅቶ ስራውን ሲጀምር፣ ሦስቱ ጄነራሎች በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች በመመደብ አገራቸውን ማገልገል ጀመሩ። ጄነራል ሙሉጌታ ቡሊ የክብር ዘበኛ አዛዥነት ከደረሱ በኋላ በወቅቱ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት ውስጥ በተፈጠረው የፖለቲካ ሽኩቻ ከቦታው ተነስተው የህዝባዊ ኑሮ እድገት ሚኒስትር ሆኑ፡፡ ጄነራል ከበደ የምድር ጦር ዋና አዛዥ ሆኑ፡፡ ጄነራል መንግስቱ ደግሞ ሙሉጌታን በመተካት የክብር ዘበኛ አዛዥ ሆኑ፡፡ ለሚያውቃቸው ሁሉ የሶስቱ ጄነራሎች ጓደኝነት ጥብቅ ነበር፡፡ ጓደኝነታቸው የወንድማማችነት ያህል ስለነበር ባለቤቶቻቸውም ሆኑ ልጆቻቸው ችግር ሲገጥማቸው በቀጥታ በመሄድ ችግራቸውን የሚያካፍሉት ለነሱ ነበር።
1953 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወሳኝ ዓመት ነበረች። ለሶስቱ ጄነራሎች ደግሞ የበለጠ፡፡ ያ ሁሉ ከልጅነት ጀምሮ በስደትና በነፃነት፣ በኋላም በነበራቸው ጥብቅ ግንኙነት የተፈጠረው ወንድማማችነት ውኃ በላው። ጄነራል መንግስቱ መንግስት ገልባጭ፣ ጄነራል ከበደ ግልበጣውን አክሻፊ፣ ጄነራል ሙሉጌታ ደግሞ ታሳሪ ሆነው አረፉት፡፡  በዚህ የተነሳም ጄነራል መንግስቱ ግልበጣው ሲከሽፍ በስቅላት ሲገደሉ፣ ጄነራል ሙሉጌታ ደግሞ በጥይት ተደብድበው ሞቱ። ለጊዜው ከሞት የተረፉት ጄነራል ከበደ ገብሬ የመጀመሪያው የተባበሩት መንግስታትን ጦር በኮንጎ የመሩ ጥቁር ጄነራል ሆኑ፡፡ በስራቸው የስዊዲን የአየር ላንድና የአንድ ጄነራሎች ገበሩ፡፡ ከዚያም የመከላከያ ሚኒስቴር በመሆን አገራቸውን አገለገሉ፡፡ በ1966 ወታደራዊው መንግስት ታላላቅ ኢትዮጵያውን የሚገኙበት ባለስልጣኖችን በግድያ ሲቀጣ፣ ጄነራል ከበደ ገብሬም በጥይት ተደብድበው ተገደሉ፡፡
ይቺ ትንሽ ታሪክ የኢትዮጵያን ምስቅልቅል ህይወት በጥቂቱም ቢሆን ታመላክታለች፡፡ የሦስቱም ጓደኛሞች ፍፃሜ ግን አይገርምም፡፡ የሳምንት ሰው ይበለን፡፡

Source/addisadmas.com

Posted by/Lemlem Kebede

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s