ሰበር ዜና – የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ የተፃረረው የፓትርያርኩ የአድባራት አለቆች ዝውውር ቁጣ ቀሰቀሰ፤ አዲሱ የደ/ጽጌ ቅ/ዑራኤል አስተዳዳሪ በሕዝቡ ተቃውሞ አቀባበል ሳይደረግላቸው ተመለሱ

  • ቋሚ ሲኖዶሱ የካህናቱንና ምእመናኑን አቤቱታ በመቀበልና የፓትርያርኩ ጥያቄ እንዲጣራ በማዘዝ፣ በሓላፊነታቸው እንዲቀጥሉ የወሰነላቸው ውጤታማው የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ ገብረ ጻድቅ፣ ውሳኔውን የሚፃረር የዝውውር ደብዳቤ በአባ ማትያስ ትእዛዝ ተጽፎባቸዋል፡፡
  • የፓትርያርኩን አግባብነት የሌለው ትእዛዝ በመቃወም የደብሩን ሀብት ከአማሳኞች ሰንሰለታዊ ምዝበራ ለመከላከል እንዲሁም የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ በማስከበር የደብሩን ሰላም ለማስጠበቅ መንፈሳዊነት በተሞላው አኳኋን የሚንቀሳቀሱ የአጥቢያው ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን በኃይል ለማስፈራራት ሙከራ እየተደረገ ስለመኾኑ ተመልክቷል፡፡
  • የአጥቢያው ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን፡- ውጤታማው አስተዳዳሪ አግባብነት በሌለው የፓትርያርኩ ትእዛዝ መነሣታቸውን በመቃወም ስላቀረቡት አቤቱታ፣ ለቦሌ ክ/ከተማ ካራማራ ንኡስ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝተው ለክፍለ ከተማው አዛዥና ለጸጥታ ሰዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
  • ጥያቄአቸው÷ በሕጋዊ ውሳኔ ተመድበው በሰላማዊ መንገድ እየመሯቸው የሚገኙት ውጤታማው አስተዳዳሪ ስለተነሡበት የፓትርያርኩ ትእዛዝ በማስረጃ የተደገፈ ምላሽ እንዲሰጣቸው መኾኑን አመልካቾቹ ገልጸዋል፡፡
  • ፀረ – የአማሳኞች ሰንሰለታዊ ምዝበራ የኾነውን ሰላማዊ እንቅስቃሴአቸውን ግለሰባዊና ፖለቲካዊ በማስመሰል ከመንግሥት ለማጋጨትና የኃይል ርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚደረግ ግፊት እንዳለ የጠቀሱት የደብሩ ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን÷ ‹‹ወደ ፖሊቲካ ይቀይሩብናል፤ እኛ ግን ፖሊቲከኞች አይደለንም›› ብለዋል፡፡
  • የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በሚፃረረው የፓትርያርኩ ትእዛዝ ከሳሪስ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ተዛውረው በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን የተመደቡት አለቃ፣ ‹‹ወደ ደብሩ መሔድ የሚገባቸው ከሰበካ ጉባኤው አስተዳደር ጋራ አስቀድመው ከተነጋገሩና ከተግባቡ ብቻ እንደኾነ›› በትላንት ዕለት ከፖሊስ ተነግሯቸው እንደነበር ተገልጧል፡፡፡

*                   *                  *

  • የአጥቢያው ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን የደብሩን ሰላምና ሀብት ከአማሳኞች የምዝበራ ሰንሰለት ለመጠበቅና የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ለማስከበር የሚያደርጉት የተቀናጀ ጥረት÷ ከቋሚ ሲኖዶሱ፣ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳት፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎችና ከሌሎችም አጥቢያዎች ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገለት ነው፡፡
  • ውጤታማና የብዙኃን ተቀባይነት ያላቸውን አለቆች፣ በጥቅመኝነት በታወረው የአማሳኞች ምክር ማዘዋወርን የመረጡት አባ ማትያስ፣ ቋሚ ሲኖዶሱ ያልተቀበለውን የዝውውር አቋማቸውን በባለሥልጣናት ጉልበት እና በአማሳኞች ተንኰል ለማስፈጸም መንቀሳቅሳቸውን ቀጥለዋል፡፡
  • ፓትርያርኩ÷ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት አድርገው ከቋሚ ሲኖዶሱ ጋራ እየተወያዩ ከመሥራት ይልቅ ‹‹አለቆችን በራሴ ፍላጎት ብቻ የማዘዋወር ሥልጣን ከሌለኝ ፓትርያርክነቴ ምንድን ነው?›› ሲሉ ለባለሥልጣናት አቤቱታ ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡
  • ለአቋማቸው ተቀባይነት አለማግኘትና ላስከተለው ከፍተኛ ተቃውሞ ማኅበረ ቅዱሳንን ተጠያቂ ለማድረግ በአማሳኞች አመቻችነት ከሚገናኟቸው ባለሥልጣናት ጋራ መክረዋል፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊ ኾነው አላሠራ አሉኝ፤›› በሚል በማኅበሩ ላይ ጫናቸውን ለማጠናከርም እየተዘጋጁ ነው ተብሏል፡፡

*                   *                  *

St. Urael parish head row02በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ዛሬ ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ከእሑድ ሰንበት ጸሎተ ቅዳሴ መጠናቀቅ በኋላ የደብሩ ካህናት፣ ሠራተኞች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና በርካታ ምእመናን ውጤታማው የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ ገብረ ጻድቅ ወደ ሌላ ደብር መዛወራቸውን በተመለከተ ተቃውሟቸውን ሰላማዊነት በተሞላው አኳኋን ሲያሰሙ ውለዋል፡፡

በተቃውሞው እንደተገለጸው÷ ከሐምሌ ወር ፳፻፫ ዓ.ም. ጀምሮ ካህናትና ምእመናን በአንድ ቃል በሚመሰክሩለት የተሟላ ክህነታዊ አገልግሎትና ብቃት ያለው አስተዳደራዊ ክህሎት ደብሩን የመሩትና በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ፋይናንሳዊ ሀብቱን ከአማሳኞች የምዝበራ ሰንሰለት ጠብቀው ከፍተኛ የልማት አቅም በመፍጠር መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ ገብረ ጻድቅ እስከ ዛሬ ከታዩት አለቆች ኹሉ ይልቅ ውጤታማ ኾነዋል፡፡

ውጤታማው አስተዳዳሪ፣ ከሰበካ ጉባኤው ጋራ በመተባበር÷ በስብከተ ወንጌል፣ በመልካም አስተዳደር እና በልማት መስኮች ያሳዩት የአገልግሎት ፍሬ በሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ጭምር መረጋገጡን በተቃውሞው ተመልክቷል፡፡

ውጤታማው አስተዳዳሪ ዓመት ሳይሞላቸው ለደብሩ በፈጠሩት ከፍተኛ አቅም የያዟቸውን ዕቅዶች ተግባራዊ ለማድረግ ዕድል ሊሰጣቸው የሚገባ እንጂ የአጥቢያውን ሀብት እንደለመዱት ለመቀራመት ባሰፈሰፉና በፓትርያርኩ ዙሪያ በተሰለፉ አማሳኞች ምክር ሊነሡ እንደማይገባ በብርቱ ተጠይቋል፡፡

በፓትርያርኩ ዙሪያ የተሰለፉ አማሳኞች ከደብሩ ልማደኛ መዝባሪዎች ጋራ ሰንሰለታዊ ግንኙነት በመፍጠር የፈበረኩት ክሥ፣ ባለፈው ረቡዕ፣ ሰኔ ፳፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በተካሔደው የቋሚ ሲኖዶሱ ሳምንታዊ ስብሰባ ላይ በፓትርያርኩ አማካይነት እንዲያው በደፈናው ቀርቦ እንደነበር ተገልጧል፡፡

ይኹንና ክሡ አንድም ፓትርያርኩ በደፈናው ተቀበሉኝ ያሉትን የፈጠራ ክሥ በማስረጃ ማስደገፍ ባለመቻላቸው፣ በሌላም በኩል ከፓትርያርኩ የስማ በለው ክሥ ይልቅ የተቋማዊ ለውጥ ጥናቱ አጋር የኾኑት አስተዳዳሪ በስብከተ ወንጌል፣ በመልካም አስተዳደርና በልማት ስላደረጉት ውጤታማ ጥረት በቅርበት የሚያውቀው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በቃለ ጉባኤ አስደገፎ ከሰጠውና ቅ/ሲኖዶሱ በንባብ ካዳመጠው ምስክርነት ጋራ በቀጥታ የሚፃረር በመኾኑ በተባበረ ድምፅ ውድቅ ተደርጓል፡፡

የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ለቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መነሻ እንዲኾን በፓትርያርኩ ትእዛዝ ሠርቶ ያቀረበው የዝውውር ቃለ ጉባኤ÷ አጥቢያው ከኹለ ገብ ሕንጻው የኪራይ ውል፣ ከሙዳይ ምጽዋትና ሌሎች በርካታ የገቢ ምንጮቹ በተጭበረበሩ ሰነዶች ከ22 ሚልዮን ብር በተመዘበረበትና ሰላሙ በታወከበት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ከደብረ ነጎድጓድ ቅ/ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ተዛውረው የተመደቡት መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ፣ደብሩን ከማረጋጋትም በላይ በአጭር ጊዜ በስብከተ ወንጌል፣ በመልካም አስተዳደርና በልማት እንዳስመዘገቡት የዘረዘረው የሥራ ፍሬ የሚያስመሰግን እንጂ ከሓላፊነት የሚያሥነሳ ኾኖ እንዳላገኘው ቋሚ ሲኖዶሱ መወያየቱ ተጠቅሷል፡፡

አቡነ ማትያስ÷ አለቃውን በማንሣትና በቀጣይ በሚካሔደው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ምርጫ አጋጣሚ አስተዳደሩን በመቆጣጠር በጥንቃቄ የተጠበቀውን የአጥቢያውን ቅምጥ ሀብት የመቀራመት ዕቅድ ያላቸው የደብሩ ልማደኛ መዝባሪዎች፣ በዙሪያቸው ከተሰለፉ አማሳኞች ጋራ የሸረቡትን ተንኰል ከመቀበላቸው በፊት በሐሰት ተከሣሹን አስተዳዳሪ በሚገባ አቅርበው ያውቋቸው እንደኾነ በቋሚ ሲኖዶሱ አባላት ጥያቄ እንደቀረበላቸውም ተዘግቧል፡፡

አለቃው እንዲነሡ በፓትርያርኩ የተያዘው አቋም ተቀባይነት የሚኖረው በበቀልና በጥቅመኝነት ስሜት መቅረቡ የታመነው የአማሳኞች ክሥ ልዩ ሀገረ ስብከቴ ነው ከሚሉት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ከቀረበው የአስተዳዳሪው ዘርፈ ብዙ የውጤታማነት ምስክርነት ጋራ ተነፃፅሮ ሐቀኝነቱ ሲረጋገጥ ብቻ መኾኑን ቋሚ ሲኖዶሱ በውሳኔው አመልክቷል፤ እስከዚያው ድረስ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ለቋሚ ሲኖዶሱ ቀርበው በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ የተመደቡት ውጤታማው አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ ገብረ ጻድቅ በምደባቸው ጸንተው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ በሙሉ ድምፅ መወሰኑ ታውቋል፡፡

ፓትርያርኩ ግን በውሳኔው የተስማሙ መስለው በወጡ ማግሥት፣ አስተዳዳሪው ወደ ሳሪስ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን እንዲዛወሩና አዛውንቱ የሳሪስ አለቃም ወደ ደብረ ጽጌ ቅ/ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን እንዲሔዱ ትእዛዝ አስተላልፈዋል፤ ትእዛዙም በልዩ ጽ/ቤታቸው የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ፊርማ ለየአለቆቹ በተከታታይ ቀናት መድረሱ ተገልጧል፡፡

St. Urael parish head row01

ደብዳቤው ለበርካታ የመንግሥት አካላት ግልባጭ መደረጉ የተገለጸ ሲኾን ይህም ፓትርያርኩ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ተደግፎ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋራ እየተወያዩ የተስማሙበትን ውሳኔውን ከማስፈጸም ይልቅ በጥቂት አማሳኞች የክፋት ምክር መመራትንና በባለሥልጣናት ጉልበት መመካትን መምረጣቸውን እንደገፉበት ያጠይቃል ብለዋል፤ ምእመናኑ በተቃውሟቸው፡፡

አኹንም ጥያቄአቸው የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ማስከበርና አስተዳዳሪው ከሓላፊነታቸው አላግባብ የሚነሡበት ምክንያት ግልጽ እንዲደረግልን ነውየሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎች፣ አለቃውን በሥራቸው ከሚያውቋቸውና በውጤታማነታቸው ከሚደግፏቸው በቀር ግለሰባዊ ጉዳይ እንደሌላቸው ገልጸዋል፤ እንቅስቃሴቸው ፀረ ሰላምና ፖለቲካዊ ነው በሚል ከመንግሥት ጋራ ለማጋጨት የሚሰነዘረው ትችትም አገልጋዩና ምእመኑ መብቱን እንዳይጠይቅና እናት ቤተ ክርስቲያኑን እንዳይጠብቅ ለማሸማቀቅ ያለመ የአማሳኞች የተለመደ ተንኰል ነው ብለዋል፡፡

አስተዳዳሪው በማስረጃ ተደግፎ የሚቀርብ ጥፋት ካለባቸው፣ በአማሳኞች የምዝበራ ሰንሰለታዊ አሠራር እንደተለመደው፣ ከደብር ደብር ከማዘዋወር ይልቅ በሓላፊነት ቦታ ከመቀመጥ ታግደው በሕግ መጠየቃቸውን እንደሚመርጡ፣ ይህም በደብሩ መዋቅር በተለያየ የሓላፊነት ደረጃ የመሸጉና በዓይነ ቊራኛ የሚከታተሏቸውን ልማደኛ መዝባሪዎችን ጭምር ማካተት እንደሚኖርበት ለዚኽም በግንባር ቀደምነት እንደሚሰለፉ ተናግረዋል፤ ምእመኑ በየአጥቢያው ምዝበራን ለመዋጋት ከአማሳኞች ጋራ የሚፈጥረውን ግጭት ለመፍታት በሚል እንደፈሊጥ የተያዘው ያለተጠያቂነት የማዘዋወር አሠራርም መታረም እንዳለበት አሳስበዋል – ‹‹ሌላውስ ደብር የአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን አካል አይደለም ወይ? ለዘራፊዎች ለምን ተጨማሪ ዕድል ይሰጣቸዋል?›› በማለትም ይጠይቃሉ፡፡

St. Urael parish head row00ካህናቱ፣ የጽ/ቤት ሠራተኞቹና ምእመናኑ በዛሬው የእሑድ ሰንበት ረፋድ ተቃውሞው የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በሚፃረረው የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ደብዳቤ መነሻነት በተላለፈላቸው ሕገ ወጥ የዝውውር ትእዛዝ ማልደው የመጡትን አረጋዊውን የሳሪስ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አባትነት አክብሮ ነገር ግን መመደባቸውን ሳይቀበል በጨዋነት መልሷቸዋል፤ የሚከተለውን ማሳሰቢያም ከዐውደ ምሕረቱ ተሰጥቷል – ‹‹ጥያቄአችን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይከበር የሚል እንጂ የአንድ አለቃ መነሣት አይደለም፤ እርስዎን አባታችንን እናከብርዎታለን፤ ጥያቄአችን በአግባቡ እስኪመለስ ድረስ ግን እንዳይመጡ፡፡››

ከቁጥሩ ብዛት ጋራ መንፈሳዊነትና ሰላማዊነት የታየበት የአገልጋዩና ምእመናኑ የተቀናጀ የተቃውሞ ሥርዓት በደብሩ የተገኙትን ስቭል ለባሽ የጸጥታ ሰዎችና የፖሊስ ኃይሎች ጭምር ያስደመመ ነበር፡፡ የአማሳኞች መቅሠፍት፣ የመናፍቃን ውጋት በመኾን የታወቁት የአጥቢያው ወጣቶችና ወላጆች ምእመናን በወቅቱ በኅብረት ካሰሟቸው መዝሙራት መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፤

ተዋሕዶ ሃይማኖቴ፣
የጥንት ነሽ የናትና አባቴ፤

ማዕተቤን አልበጥስም፣
ትኖራለች ለዘላለም፤

አንመካም በጉልበታችን
እግዚአብሔር ነው የኛ ኃይላችን፡፡

ይኹንና ዘግይተው የደረሱ በቁጥር እስከ አርባ የሚገመቱ የፌዴራል ፖሊሶች ሦስቱንም የቤተ ክርስቲያኑን በሮች በመዝጋት ዙሪያውን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ የክ/ከተማው ኮማንደር ናቸው በተባሉና በደብሩ ውስጥ በስቭል ልብስ በቆዩ አዛዥ ትእዛዝ እንዲመለሱ መደረጋቸው ታውቋል፡፡

በፓትርያርኩ የተመደቡት አስተዳዳሪ በመጡበት አኳኋን ተቀባይ ሳያገኙ መመለሳቸውን ተከትሎ ከሠርሆተ ሕዝብ ከተደረገ በኋላ ሰባት ያህል ካህናት፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የጽ/ቤት ሠራተኞች፣ የሰንበት ት/ቤት አባላትና ምእመናን ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ካራማራ ንኡስ ፖሊስ ጣቢያ ተጠርተው መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡

ለሰላም ሲባል አስተዳዳሪው ለዛሬው አቀባበል ከመሔዳቸው በፊት ከሰበካ ጉባኤው ጋራ አስቀድሞ መነጋገርና መግባባት እንደሚጠበቅባቸው ትላንት ማምሻውን ከፖሊስ ማሳሳቢያ ደርሷቸው እንደነበር በንግግሩ ተጠቅሷል፤ የዝውውር ውሳኔው በፓትርያርኩ እንደታዘዘ በመጥቀስ አስተዳዳሪውን እንዲቀበሉ ለማድረግ ከፖሊስ በኩል የተደረገው ሙከራ ግን ትእዛዙ አግባብነት እንደሌለው በሚገልጽና እንቅስቃሴው ተገቢ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ መንፈሳዊነቱንና ሰላማዊነቱን ጠብቆ እንደሚቀጥል በሚያመለክት ማብራሪያ ምላሽ እንደተሰጠበት ታውቋል፡፡

Source/haratewahido.com

Posted by/Lemlem Kebede

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s