የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በፓትርያርኩ እና ጳጳሳቱ ፍጥጫ ተቋጨ

  • ጳጳሳት የፓትርያርኩን የማኅበረ ቅዱሳን ደንብ ማሻሻያ ቅድመ ኹኔታ አልተቀበሉትም
  • ‹‹ቅድመ ኹኔታው የማኅበሩን አገልግሎት የሚያቀጭጭ በሒደትም የሚያስቆም ነው፡፡›› /ታዛቢዎች/
  • ማኅበሩ የመተዳደርያ ደንቡ ማሻሻያ ረቂቅ እስኪጸድቅ በነባሩ ለመመራት ይገደዳል

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፫ ቁጥር ፯፻፶፤ ቅዳሜ ግንቦት ፳፫ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)

Holy Synod endingበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅን እንደ አንድ አጀንዳ የያዘው የዘንድሮው የቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ከረቂቁ ጋራ በተያያዘ በፓትርያርኩ እና በሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል በተፈጠረ ፍጥጫ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

የፍጥጫው መንሥኤ፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ የተሠየመው የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደርያ ደንብ አጥኚ ኮሚቴ ያዘጋጀው የማሻሻያ ረቂቅ በዝርዝር ከመታየቱ አስቀድሞ ፓትርያርኩ ለውይይቱ እንደ ቅድመ ኹኔታ ያቀረቧቸው ነጥቦች በአብዛኛው የምልዓተ ጉባኤው አባላት የገጠመው ተቃውሞ እንደኾነ የስብሰባው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

የቅ/ሲኖዶሱን ስብሰባ በርእሰ ጉባኤነት የሚመሩት ፓትርያርኩ፣ በአጀንዳው ላይ የሚካሔደውን ውይይት ቀጣይነት ይወስናል በሚል ካቀረቧቸው ቅድመ ኹኔታዎች ውስጥ÷ ለአጥኚ ኮሚቴው መመሪያ የሰጡባቸው ‹‹ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች›› አንድም ሳይቀነሱ በደንቡ እንዲካተቱና ረቂቁ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ከጸደቀ በኋላ እንዲታይ የሚሉ እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡

ፓትርያርኩ በቅድመ ኹኔታ አስቀምጠዋቸዋል በተባሉት ነጥቦች ስምምነት ላይ ከተደረሰ ስብሰባው ሊቀጥል እንደሚችል በመጥቀስ የምልዓተ ጉባኤውን ድጋፍ ኃይለ ቃልም ተማኅፅኖም በተቀላቀለበት አኳኋን መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡

ይኹንና የሚበዙት ሊቃነ ጳጳሳት በቀጥታ እንደተቃወሟቸው፣ የተቀሩትም ለፓትርያርኩ ድጋፍ ከመስጠት እንደተቆጠቡ ታውቋል፡፡ ፍጥጫው ቀጥሎ አቡነ ማትያስ ‹‹አቋሜ ይኽው ነው፤›› በሚል አጀንዳውን መዝጋታቸውን ሲያስታውቁም፣ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ እንዲህ ተብሎ የሚተው አይደለም፤›› በሚል ከኹሉም ሊቃነ ጳጳሳት ጠንካራ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ምንጮቹ ይገልጻሉ፡፡

የቅ/ሲኖዶሱ መደበኛ ስብሰባ የሚካሔደው ምልዓተ ጉባኤው ከጅምሩ ተስማምቶ ባጸደቃቸው የመነጋገርያ አጀንዳዎች መሠረት እንደኾነ በሊቃነ ጳጳሳቱ ተቃውሞ ተጠቅሷል፡፡

የማኅበሩ የመተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ እንዲቀርብ ከሚጠበቅበት ከጥቅምት ፳፻፭ ዓ.ም. ጀምሮ* እየተንከባለለ ለኹለት ዓመታት መዘግየቱን ሊቃነ ጳጳሳቱ አስታውሰው፣ የተጓተተው አጀንዳ ‹‹የማኅበሩን አገልግሎት ያቀጭጫሉ፣ በሒደትም ያስቆማሉ›› በሚል በተተቹት የፓትርያርኩ ቅድመ ኹኔታዎች ሊዘጋ እንደማይችልና ተጨማሪ ጊዜ ሳይወስድ ቅ/ሲኖዶሱ ሊወያይበት እንደሚገባ በአጽንዖት በመናገራቸው፣ አጀንዳው መታየት በጀመረበት ቀን ሳይቋጭ ለቀጣዩ ቀን በይደር ተላልፏል፡፡

አጀንዳው ሰኞ፣ ግንቦት ፲፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ጥዋት መታየት ሲጀምር፣ አጥኚ ኮሚቴው በ37 አንቀጾችና በ34 ገጾች አሻሽሎ ያዘጋጀው የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብና የኮሚቴው ቃለ ጉባኤ በንባብ መሰማቱ ታውቋል፡፡ ፓትርያርኩ ‹‹ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች›› በሚል ራሱን በቻለ ርእስ በደንቡ እንዲካተት ለአጥኚ ኮሚቴው ጥብቅ መመሪያ የሰጡበት ባለ24 አንቀጽ ሰነድም አብሮ እንዲነበብላቸው የጠየቁበት ኹኔታም የመጀመሪያ ቀን የፍጥጫ መነሻ እንደነበር ተሰምቷል፡፡

በ24 አንቀጾችና በአምስት ገጾች የተዘረዘሩት የፓትርያርኩ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች÷ በአባላቱ በጎ ፈቃድ ተቋቁሞ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ የሚገኘውን ማኅበር ከሕገ ተፈጥሮው ውጭ የሚያደርግ፣ በቅ/ሲኖዶሱ ፈቃድ ከሚመራበት ደንብ በተፃራሪ ተቋማዊ ህልውናውን፣ የአመራር ምርጫውን፣ የአባላት አያያዙንና የሥራ ቦታውን ለውጭ ተጽዕኖ አሳልፎ የሚሰጥና አጣብቂኝ ውስጥ የሚያስገባ፣ በአርኣያነት የሚጠቀሰውን የፋይናንስ አሠራሩን ወደ ኋላ የሚጎትት መኾኑን እንደተረዱ ያብራሩ አንድ የቅ/ሲኖዶሱ አባል፣ ‹‹ቀጣዩ ቀንም የከበደ ነገር ይዞ እንደሚመጣ ግልጽ ነበር፤›› ይላሉ፡፡

በይደር የተያዘው አጀንዳ በቀጣዩ ቀን ማክሰኞ ጥዋት ተጀምሮ ለግማሽ ቀን የቀጠለ ቢኾንም ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ የመተዳደርያ ደንብ ማሻሻያውን ወደ ዝርዝሩ ገብቶ ለመመልከት የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ እንዳልተቻላቸው ታውቋል፡፡

His Holiness Ab Mathias01‹‹ፓትርያርኩ በቅድመ ኹኔታ ያስቀመጧቸውን ነጥቦችና በአጀንዳው ቀጣይነት ላይ የያዙትን አቋም አልቀየሩም፤ ሊቃነ ጳጳሳቱም ባጸደቅነው አጀንዳ መሠረት ቅድሚያ ሰጥተን መነጋገር ያለብን የሠየምነው አጥኚ ኮሚቴ አዘጋጅቶ ባቀረበው ረቂቅ ላይ ነው፤ መካተት ያለበት ነገር ካለም ማኅበሩን በሚያሠራ መልኩ እያገናዘብን በሒደት እናየዋለን እንጂ አጀንዳው በቅድሚያ ኹኔታ መታሰር የለበትም በሚል በተለያዩ አግባቦች ለማስረዳት ጣሩ፤ በመጨረሻም ፓትርያርኩ‹እንግዲያውስ ስብሰባውን ለመምራት አልችልም› በማለታቸው የስብሰባው መቋጫ ኾኗል፤›› ይላሉ – ሒደቱን ለአዲስ አድማስ የገለጹ የስብሰባው ምንጮች፡፡

የማኅበሩ ደንብ በመጀመሪያ ረድፍ ከሰፈሩት የቅ/ሲኖዶሱ መነጋገርያ ነጥቦች አንዱ እንደነበር ያስተዋሉ ሌሎች የስብሰባው ተከታታዮች በበኩላቸው፣ አጀንዳው ከቅደም ተከተሉ ወጥቶ እየተገፋ በመጨረሻ መነሣቱ በፓትርያርኩና በሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል ይህ ዓይነቱ አለመግባባት ሊነሣ እንደሚችል ጠቋሚ ነበር ብለዋል፡፡

ተከታታዮቹ አክለውም፣ ፓትርያርኩ ስብሰባውን ለመምራት ፈቃደኛ ባይኾኑም በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ በተደነገገው የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት መሠረት፣ ምልዓተ ጉባኤው በማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያዎች ላይ የጀመረውን ውይይት ቀጥሎ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚችልባቸው አግባቦች እንደነበሩ ገልጸው፣ ቅ/ሲኖዶሱ በጋዜጣዊ መግለጫው፣ የመጨረሻው መነጋገርያው ባደረገው የማኅበሩ ደንብ ላይ ‹‹ውይይት ተደርጎበታል›› ከማለት በስተቀር አጀንዳውን ያለውሳኔ የቋጨበት አኳኋን ያልተለመደና አደናጋሪ ነው ብለዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በዘመኑ ጥበብ የሠለጠነውን ኦርቶዶክሳዊ ትውልድ አደራጅቶ ማንነቱን የሚያውቅበትንና በግብረ ገብ የሚታነፅበትን ትምህርተ ሃይማኖት ከማስተማር ባሻገር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት አገልግሎታቸውን በብቃት የሚወጡበትን ኹለገብ ሞያዊ ድጋፍ የመስጠት ሓላፊነት እንዳለበት በደንብ አጥኚ ኮሚቴው የማሻሻያ ረቂቅ ላይ መስፈሩ ተገልጧል፡፡

ይኹንና ‹‹ጥበቃና ጥንቃቄ›› በሚል ፓትርያርኩ እንደ መመሪያ ያቀረቧቸው ድንጋጌዎችና ግዴታዎች እንዲሁም ከልዩ ጽ/ቤታቸው ማኅበሩን አስመልክቶ በየጊዜው የሚወጡ መመሪያዎች የማኅበሩን አገልግሎት የማቀጨጭ በሒደትም አዳክሞ የማስቆም ውጤት ሊኖራቸው እንደሚችል የጉዳዩ ተከታታዮች ስጋታቸውን ያስረዳሉ፡፡

የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ፣ ቅ/ሲኖዶሱ የማኅበሩ ደንብ እንዲሻሻል ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. ባካሔደው ስብሰባ**÷ ማኅበሩ፣ ከጊዜው ጋራ የሚሔድ፣ አገልግሎቱና አደረጃጀቱ የደረሰበትን ስፋትና ዕድገት የሚመጥን፣ ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ልማት የሚጠቅም ድርጅታዊ መዋቅር እንደሚያስፈልገው ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት አምስት ሊቃነ ጳጳሳት፣ ገለልተኛ የሕግ ባለሞያዎችና የማኅበሩ አባላት በታከሉበት አጥኚ ኮሚቴ የጋራ ጥናት የተዘጋጀ መኾኑ ታውቋል፡፡

በግንቦት ወር ፲፱፻፹፬ ዓ.ም. በበጎ ፈቃድ በተሰበሰቡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ማኅበረ ካህናት የተመሠረተው ማኅበሩ፤ እየተመራ የሚገኘው ቅ/ሲኖዶስ በሐምሌ ወር ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ አሻሽሎና በሙሉ ድምፅ አጽድቆ በሰጠው መተዳደርያ ደንብ ሲኾን ለአራተኛ ጊዜ የተሻሻለው ረቂቅ በወቅቱ ተመርምሮ ባለመጽደቁ በነባሩ ደንቡ እየተመራ ለመቀጠል እንደሚገደድ ተመልክቷል፡፡

Source/www..ethiopianreview.com

Posted by/Lemlem Kebede

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s