በግንቦት 20 ዋዜማ ኢህአዴግ ምን ይላል?

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የህዝብ ተሳትፎ እና አደረጃጀት ሚኒስትር ዴኤታ እና የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽ/ቤት የህዝብና ውጭ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ 
አቶ ደስታ ተስፋው፤ 23ኛው የግንቦት 20 በዓልን ጨምሮ በወቅታዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡   

በ23ኛው የግንቦት 20 በዓል፣ ኢህአዴግ እንደስኬት የሚገልፃቸውን ሊነግሩን ይችላሉ?
በ1983 ዓ.ም የደርግ ስርዓት ሲደመሰስ ኢትዮጵያ ወደ መበታተን የደረሰችበት፤ ኢኮኖሚው በከፍተኛ ደረጃ የወደቀበትና አገሪቱ ህልውናዋ አደጋ ውስጥ የገባበት ወቅት ነበር፡፡ በእነዚህ 23 ዓመታት በርካታ ስኬቶች አግኝተናል፡፡ ኢትዮጵያ ትበታተናለች፣ እንደ ሶማሊያና ዩጐዝላቪያ ትሆናለች፤ የሚባለውን ቀልብሰን የሽግግር መንግስት በማቋቋም፣ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ያሉበት፣ አገሪቱን የቀጣይ ህገመንግስት ባለቤት የማድረግ የተሳካ የሽግግር ጊዜ ተከናውኗል፡፡ 
የሀገራችን ብሔሮችና ብሔረሰቦች በራሳቸው ፍላጎት ያፀደቁት፣ የብሄር ብሄረሰቦችን መብቶች የሚያስከብር፣ የግለሰቦችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ ነፃነቶች በአግባቡ የያዘ ዲሞክራሲያዊ ህገመንግስት ባለቤት መሆናችን፣ ዋነኛ ስኬትና መሠረት ተደርጐ ይወሰዳል፡፡
ሌላው በኢኮኖሚው ዘርፍ ያስመዘገበንው ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ አስር አገሮች አንዷ ሆናለች፡፡ ይሄ ፈጣን ኢኮኖሚ በአለፉት አስር ዓመታት በአማካይ ባለሁለት አሃዝ እድገት እያስመዘገበ የመጣ ቀጣይነት ያለው እድገት ነው፡፡ ይሄ እድገት ፈጣን ብቻ ሳይሆን ተከታታይም ነው፡፡ ተከታታይም ብቻ ሳይሆን የህዝቦችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው፡፡ የዜጐች የነፍስ ወከፍ ገቢ እያደገ ነው፤ 550 ዶላር ደርሷል፡፡ ድህነትም እየቀነሰ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው ወደ 26 በመቶ ዝቅ ያለበት፣ ከሱም በታች የወረደበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ከዲሞክራሲ ግንባታ አኳያ ያገኘናቸው ስኬቶችም አሉ፡፡ በኢትዮጵያ  በምርጫ ስልጣን የሚያዝበት ህገመንግስታዊ ስርዓት ተፈጥሮ፣ ባለፉት ዓመታት አራት አገራዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ እነዚህ አገራዊ ምርጫዎች፤ ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊና አሳታፊ በሆነ ሁኔታ የተከናወኑ ናቸው፡፡ በምርጫዎቹም ህዝቡ በነቂስ እየወጣ ይሆነኛል የሚለውን በካርዱ የሚመርጥባት አገር ሆናለች፡፡ ስልጣን በጠብመንጃ አፈ ሙዝ የሚያዝባት ሳትሆን፣  በህዝብ በተመረጠ መንግስት የምትተዳደር አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ 
የፌደራላዊ ስርዓታችን፣ የኢትዮጵያን ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጥቅምና መብት በማስከበር፣ በተለይ የህዝብን ተሳትፎ እስከ ታች ድረስ ባረጋገጠ መንገድ ከፍተኛ የሆነ ውጤት እየተመዘገበበት ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች፤ ከምንጊዜውም በላይ ጠንካራ አንድነታቸውን እየገነቡ ነው፡፡ 
ህዝቡ በኢትዮ – ኤርትራ ጦርነት ጊዜ፣ ከዳር እስከ ዳር ተነስቶ ያበረከተው አስተዋጽኦ፤ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረገው ያለው የድጋፍ እንቅስቃሴ እንዲሁም አገሩን ተረባርቦ ለማሳደግ የሚያሳየው ትጋት ሌላው ስኬታችን ነው፡፡ በሰላም ረገድ ኢትዮጵያ በሰላም እጦት የምትቸገር አገር ነበረች፡፡ ይሄ የሰላም እጦት ሙሉ በሙሉ ተወግዶ፣ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት አገር ሆናለች፡፡ ከራሷ አልፋ ለጐረቤቶቿ፣ የአፍሪካ አገራት የሰላም ተምሳሌት በመሆን አስተዋጽኦ እያበረከተች ነው፡፡ 
እርስዎ ባለፉት 23 ዓመታት እነዚህ ሁሉ ስኬቶች መገኘታቸውንና ብዙ መብቶች መከበራቸውን ገልፀዋል፡፡ ሆኖም በአገሪቱ ላይ ለ23 ዓመታት ያልተመለሱ የዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች እንዳሉ አለማቀፍ ተቋማት በተለያዩ ጊዜያት ያወጧቸው ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ ኢህአዴግ ለዚህ ምን ምላሽ አለው?
የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በራሱ ሂደት ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ገንብተን ጨርሰናል የሚባልበት ሁኔታ የለም፡፡ በማንኛውም ዓለም ዲሞክራሲ የተገነባው በሂደት ነው፡፡ በዲሞክራሲ ዳብረዋል የተባሉ አገሮች፣ አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በርካታ ዓመት ፈጅቶባቸዋል፡፡ 
እንደሚታወቀው ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በአደባባይ ከሚረገጡበት ፍፁም አምባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ ነው የወጣነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሂደታችንን ቆመን ስንመረምረው ነው ጉዞው ስኬታማ ነው ብለን የምንደመድመው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ከመንገድ ላይ ተይዞ ህይወቱን አያጣም፤ አይገረፍም፡፡ ይሄን ህዝቡ ሊመሰክረው ይችላል፡፡ 
እነዚህ አለማቀፍ ተቋማት ሪፖርቶች የሚያወጡት ከራሳቸው ፍላጐት አንፃር ነው፡፡ በስሜት ላይ የተመረኮዙና በአጠቃላይ አገሪቱን ሊጐዳ ይችላል ብለው በሚያስቡት አቅጣጫ ነው ሪፖርቶቹን የሚያወጡት፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከምንከተለው ርዕዮት አለም ጋር ይያያዛል፡፡ ኢትዮጵያ የምትከተለው ከኒዮሊበራል አማራጭ የሆነ ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ ርዕዮት ነው፡፡ ይሄ ርዕዮት አገር ቀይሯል፡፡ እየቀየረም ነው፡፡ ሁሉንም ያስደመመ ልማት እየመጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይሄ እንዲሆን የማይፈልጉ ወገኖች አሉ፡፡ 
ኢትዮጵያ እነሱ ከሚያዙላት ርዕዮታዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ውጭ መሄዷ የማያስደስታቸውና ያገኘናቸውን ስኬቶች ጥላሸት የሚቀቡ ሃይሎች አሉ፡፡ የውስጥም የውጭም ሃይሎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ኃይሎች የተቀነባበረና የአገርን ስም የሚያጐድፍ ዘገባ ነው የሚወጣው፡፡ ዘገባዎቹ ሚዛናዊ አይደሉም፡፡ ለተገኙት ስኬቶች ሁሉ ዋጋ አይሰጡም፡፡
የህብረተሰብ አስተሳሰብ እየተገነባ ባለበት ሁኔታ፣ አልፎ አልፎ የሚከሰት ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ ቀውስ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ እንኳን በማደግ ላይ ያሉ አገሮች በራሳቸውም አገር በርካታ ክፍተቶች አሉ፡፡ 
በሌላ በኩል እነዚሁ ሰዎች ልማቱን ይቀበላሉ፡፡ ለምን ብትይ ስለሚታይ ሊያስተባብሉት አልቻሉም፡፡ በሌላው ሪፖርታቸው ግን ሚዛናዊ አይደሉም፡፡ ሚዛናዊ ያልሆኑት ደግሞ ሆን ተብሎ ነው፡፡ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አለመከበራቸውን የሚያረጋግጠው ግን  የእነዚህ ድርጅቶች ሪፖርት ሳይሆን ህዝቡ ራሱ ነው፡፡ 
አለማቀፍ ተቋማት ከሚያወጧቸው ወቅታዊ ሪፖርቶች መካከል መንግስት የሚቀበላቸው የተወሠኑትን ብቻ ያውም በጐ በጐዎቹን እንጂ የሚጠቀሱ ችግሮችን በጄ ብሎ ለማዳመጥ ትዕግስቱም ሆደ ሰፊነቱም የለውም እየተባለ ይወቀሳል፡፡ ወቀሳውን እንዴት ያዩታል?
ኢህአዴግ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር መኖር አለበት ብሎ የሚያምነው የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግ ራሱን የሚያይና የሚፈትሽ ድርጅት ነው፡፡ በ1994 ዓ.ም ያካሄደውን ተሃድሶ ማየት ይቻላል፡፡ ያኔ ተሃድሶ ያካሄደው ሂዩማን ራይትስዎች ወይም አምነስቲ ኢንተርናሽናል መረጃ ስለሰጡት አይደለም፡፡ በወቅቱ ራሱን ፈትሾ ሃገሪቱን በዚህ መንገድ መምራት አይቻልም፤ ውስጣችንን ማየትና  ፓርቲው ውስጥ ያሉ ችግሮችን ነቅሰን አውጥተን ማረም አለብን ብሎ ነው፡፡ ከተሃድሶ ማግስት ጀምሮ ያለውና ከዚያ በፊት የነበረው የኢኮኖሚ፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት እንቅስቃሴና ግስጋሴ ጨርሶ አይገናኝም፡፡ ኢህአዴግ ህዝቡ ውስጥ ያሉ ብሶቶችና ችግሮች ምንድን ናቸው? እያለ በየቀኑ ሲያጠናና የህዝቡን የልብ ትርታ  ሲያዳምጥ የሚውል ድርጅት ነው፡፡ ነገር ግን በአገራችን የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ቦታውን ለልማታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ስላላስረከበ፣ በየቀኑ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ችግሮችን በሌሎች አለማቀፍ ተቋማት ግፊት ሳይሆን ኢህአዴግ በራሱ መፍታት አለብኝ ብሎ ያመነባቸውን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከሌላ ወገን ቢመጣም ገንቢ ትችቶች ከሆኑ ይቀበላል፤ ገንቢ ያልሆነ ጭፍን የጥላቻ ፖለቲካን የሚያቀነቅን ትችትን ግን አይቀበልም፡፡ ኢህአዴግ ከህዝብ ፍላጐት ውጭ ከሆነ ከባህር የወጣ አሳ ነው፡፡ ኢህአዴግ የሚኖረው በህዝብ ውስጥ ነው፡፡ ለትጥቅ ትግሉ ውጤትም የበቃው ከህዝቡ ጋር ስለነበረ ነው፡፡ ሁልጊዜ የህዝብን ፍላጐቶች ማሟላት ላይ አተኩሮ የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡ 
አለማቀፍ ተቋማት ከሚያነሷቸው ነጥቦች መካከል የዲሞክራሲ መንግስት መገለጫ የሆነው የፕሬስ ነፃነት አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ጋዜጠኞችን በማሰር፣ ወደ ሌላ አገር እንዲሰደዱና ሃሳባቸው በነፃነት መግለጽ እንዳይችሉ የምታደርግ አገር ናት ይላሉ፤ በቅርቡም በርካታ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ይጠቅሳሉ… 
የፕሬስ ነፃነት ዜጐች ሃሳባቸውን በነፃ የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ ማድረጊያ መሣሪያ ነው፤ ምክንያቱም በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ዜጐች ሃሳባቸውን የማንሸራሸር መብታቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ ሃሳብ በማያንሸራሸርበት፣ የሃሳብ ነፃነት በታፈነበት አገር ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አይቻልም፡፡ ዜጐች ሃሳባቸውን በነፃ ሊያንሸራሽሩ  የሚችሉት ደግሞ ሚዲያ ሲያገኙ ነው፡፡ ሚዲያው ለህዝቡ ተደራሽ መሆን አለበት፡፡ ሚዲያው በነፃነት መስራት የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ የፕሬስ ነፃነት እስከ ምን ድረስ ነው? የሚለው በህገመንግስታችን አንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ 6 በግልፅ ተቀምጧል፡፡ የጦርነት ቅስቀሳ፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ፣ የዜጐችን ክብርና ደህንነት የሚጥስ ፅሁፍ ወይም ዘገባ ግን አይፈቀድም፡፡ የፕሬስ ነፃነት አስፈላጊ ነው ተብሎ ስለታመነበት ህግመንግስት እስከሚፀድቅም አልተጠበቀም፡፡ ወሳኝ መብት ስለነበረ ከሽግግር መንግስቱ ቻርተር ጀምሮ በ1985 ዓ.ም የወጣውን የፕሬስ ነፃነት አዋጅ ተከትሎ በርካታ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ሆኖም በዚህ አገር የፕሬስ ነፃነት ላልተገባ ዓላማ እየዋለ ነው፡፡ በፖለቲካ አላማ ወይንም በሃይማኖት ስም ለሚካሄድ አክራሪነት እንዲሁም ህገመንግስታዊ ስርዓት ለመናድ  መሳሪያ እየሆነ ነው፡፡ ይሄም ሆኖ መንግስት ህጐቹን ተከትዬ፣ በሚወጡ ዘገባዎች ተመርኩዤ፣ ጋዜጠኞችን ልቅጣ የሚል አቅጣጫ አልተከተለም፡፡ ምክንያቱም የሚወጡት ዘገባዎች ብዙዎቹ በህግ ያስጠይቃሉ፡፡ እኛ አገር የፕሬስ ነፃነት ማለት ልቅ መብት ነው፤ የአገርንም ደህንነት፣ የህዝብንም ጥቅም፣ የግለሰቦችንም ነፃነት በሚጥስ መንገድ መካሄድ አለበት ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡
አሁን ባለንበት ሁኔታ የፕሬስ ነፃነት ተከብሯል፤ ከሰማይ በታች ሰው የፈለገውን የሚፃፍባት አገር ናት፡፡ እንግዲህ “ይሄን መንግስት በሃይል እንገልብጠው፤ እንጣለው” ብሎ ከመፃፍ በላይ ምን ይመጣል፡፡ ሌላ ምን ሊፃፍ ነው የተፈለገው? “ይሄን መንግስት ተነሱና በሃይል ጣሉት” ተብሎ እየተፃፈ ነው፡፡ 
የህትመት ውጤቶች ቁጥር ቀንሷል የሚባለውም የፕሬስ ስራ የሚጠይቀው ክህሎትና ብቃት ስላለ ነው፡፡ ምርጫ ሲመጣ የፖለቲካ ፓርቲ ልሳን ሆነው የሚመጡ የህትመት ውጤቶች አሉ፡፡ ምርጫው ሲያልቅ ይቆማሉ፡፡ የፕሬስ ነፃነት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የተቋቋሙና እስካሁንም የዘለቁ ጋዜጦችም አሉ፡፡ ሚዛናዊ አቋምና እቅድ ስላላቸው እየቀጠሉ ናቸው፡፡ 
የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን ያስራል ለተባለው በአሸባሪነት ተግባር ውስጥ የገባ ጋዜጠኛም ይሁን የመንግስት ባለስልጣን ወይም ሌላ ማንኛውም ዜጋ መጠየቁ አይቀርም፡፡ ጋዜጠኛ መሆን ከመጠየቅ የሚያድን ኢሚዩኒቲ አይደለም፡፡ ጋዜጠኛ ስለሆንክ በምንም አትጠየቅም የሚል የፕሬስ ነፃነት የለም፡፡ እነዚህ ታሰሩ የሚባሉትን በተመለከተ የታሰሩት ጋዜጠኛ ስለሆኑ አይደለም፡፡ ሌላ ወንጀል ውስጥ ስለተገኙ ነው፡፡ እነሱ በህግ ስር ናቸው፤ ህግ ውሳኔ ይሰጣቸዋል፡፡ 
ሪፖርቱን አወጣን የሚሉ ተቋማት የኒዮሊበራል አመለካከት ማስፈፀሚያ ተቋማት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ስርዓት፣ ዲሞክራሲ፣ ሰላም፣ በበጐ መንገድ አያዩትም፡፡ 
በቅርቡ ኢትዮጵያ መፈንቅለ መንግስት ከሚያሰጋቸው 45 አገሮች መካከል አንዷ ናት በሚል በ25ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጣት ሪፖርት መውጣቱም ይታወሳል..
ሪፖርቱን አንብቤያለሁ፡፡ አንድ ጥናት ሲጠና የሚወሰዱ መስፈርቶችና የጥናቱ ግብዓት ሲታይ ከፍተኛ ክፍተት ያለበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ ይሄን ያህል አገር የሚያተራምስ ነገር ይፈጠራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ነገር ግን የቀለም አብዮትን አጀንዳ የሚያደርጉ፣ ምርጫ በመጣ ቁጥር ብቅ ብቅ የሚሉ፤ ምርጫን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ወስዶ አገርን የማተራመስ አላማ ያላቸው እንዳሉ ግልፅ ነው፡፡ ይሄ ነገር እንዳይከሰት የምናደርገው ለህዝቡ በማሳወቅ ነው፡፡ የቀለም አብዮት ለማንም እንደማይጠቅም፣ በቀለም አብዮት የተለወጠ አገር እንደሌለ በማስረዳት፣ ህዝቡ ተረጋግቶ ለራሱ እንዲወስን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ህዝብ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ የዳበረ ልምድ አግኝቷል፡፡ በ1997 ዓ.ም የቀለም አብዮት ተሞክሮ አልተሳካም፡፡ አሁንም እየተሞከረ ነው፤ ግን ውጤት አይኖረውም። ምክንያቱም ምቹ ሁኔታ  የለም፡፡ ይህቺ አገር ድሃ ነበረች፡፡ በየመድረኩ በድህነቷ ትጠቀስ የነበረች አገር አሁን ደግሞ ፈጣን ልማት ላይ ናት ሲባል የማይነቃቃ ዜጋ የለም፡፡ ሌላ እኩይ አላማ ከሌለው በስተቀር፡፡ ይህቺን አገር መልሰን አዘቅጥ ውስጥ እንዳናስገባት መጠንቀቅ አለብን፤ ዲሞክራሲያችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዳበረ ነው፤ መልካም አስተዳደር ላይ የሚታዩ ችግሮችም የሚፈቱ ናቸው፡፡ ፓርቲያችን ይሄን የመታገል ፅናት አለው፡ ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት ቀድመው ግልጽ አቋም የወሰዱበትና አሁንም እየተረባረቡበት ጉዳይ ስለሆነ ለመንግስት ግልበጣ ወይም ለቀለም አብዮት የሚሆን ምቹ ሁኔታ የለም ማለት ይችላል፡፡ 
ለ2007 ዓ.ም ምርጫ የኢህአዴግ መንግስት ዝግጅት እንዴት ነው?
መንግስትና ኢህአዴግ ባለፉት ምርጫዎች ሲያደርጉት እንደነበረው፣ ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ የህዝቡ የመወሰን መብት የተከበረበት መሆን እንዳለበት ያምናሉ፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ የምንመረጠው በሰራነው ስራ መጠን ስለሆነ፤ ሥራችንን ቀጥለናል፡፡
አሁን ትኩረታችን ለሀገራችን ህዳሴ መሠረት ይጥላል ተብሎ በታሰበውና ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዳችን ሂደት ላይ ነው፡፡ እርብርባችን እዚያ ላይ ነው፡፡ ምርጫን በሚመለከት በፖሊሲያችንና በስትራቴጂያችንና ያገኘናቸው ስኬቶች ናቸው የእኛ ዋና የመመረጫ መስፈርቶቻችን፡፡ በተረፈ በምርጫው ዙሪያ ስለሚኖረን ዕቅድና ስትራቴጂ ጊዜው ሲደርስ የምናቀርበው ይሆናል፡፡ 
በእርግጥ ስራችንን ትተን ወደምርጫው እንድንገባ የሚፈልግ ሀይል አለ፡፡ በእኛ በኩል ግን ዋናው ጉዳያችን ይህቺን አገር ከድህነት ማውጣት ነው፡፡ ሰዎችን ለማስደሰት ብለን ሳይሆን ለራሳችንና ለህዝባችን ስንልም ዲሞክራሲያዊ ስርዓታችንን ማጠናከር ሌላው ትኩረታችን ነው፡፡ ስራችንን ትተን ወደ ምርጫው እንድንገባ የሚገፋፉን ሀይሎች አሉ ብዬአለሁ፡፡ እዚህም እዚያም የሚነሱ ነገሮችን በማራገብ፣ ከጀርባ ሆነው ህዝቡ ወደ ብጥብጥ እንዲገባ የመገፋፋት እንቅስቃሴዎች ታይተዋል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በኦሮሚያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ  የተከሰተውን ነገር ማየት ይቻላል፡፡ ተማሪዎች ተገቢ የሆነ ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ፤ ማንሳትም አለባቸው፡፡ ነገር ግን ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ ጉዳዩ ወደ አልሆነ አቅጣጫ ሄዶ ብጥብጥ እንዲነሳ፣ የህዝቡ ሰላም እንዲደፈርስ የማድረግ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ ይሄ የሚደረገው በዚህች መሃል በምትገኝ አጋጣሚ ስልጣን ላይ ለመውጣት የሚፈልግ ሀይል ስላለ ነው፡፡ ውጭም  ሆነው አሁን መጣን፣ ደርሰንላችኋል የሚሉ አሉ፡፡ 
የአዲስ አበባ መስተዳደርና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላንን በመቃወም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባደረጉት እንቅስቃሴ በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በዚህ የተነሳም በመንግስት በኩል የተወሰደውን የሃይል እርምጃ የሚቃወሙ አሉ፤ መንግስትም ህይወታቸውን ያጡ ተማሪዎችን አስመልክቶ ማዘኑን ገልጿል፤ የጋራ ማስተር ፕላኑ በደንብ ውይይት ሳይደረግበት ይፋ መሆኑትክክል አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ?
እንደ ኢህአዴግ ማንኛውም የልማት እቅድ ረቂቁ ይዘጋጃል፤ በረቂቅ እቅድ ላይ ውይይት ይደረግበታል። ይሄ ጉዳይ ረቂቅ የተቀናጀ የልማት እቅድ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሊደግፈውና ሊያደንቀው የሚገባ እቅድ ነው፡፡ ከተሞቹ ተያይዘው በመሰረተ ልማት ይደጉ ነው የሚለው፤ ሌላ ምንም አይልም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የሚዘረጉ መሠረተ ልማቶች የአካባቢውን ከተማሞች ይጥቀሙ ነው። ከዚህ የተለየ ነገር የለውም፡፡ የመከለል ጉዳይ አለመሆኑን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ ነገር ግን የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈፀም፤ “በፊንፊኔ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ተከለሉ”፤ “አርሶ አደሩ ሊፈናቀል ነው” የሚሉ የተሳሳቱ መረጃዎች በመስጠት ነው ተማሪዎችን ያደናገሯቸው፡፡ 
የልማት ዕቅዱ ተግባራዊ የሚሆነው የአዲስ አበባ ምክር ቤትና የየአካባቢው ምክር ቤቶች ሲያፀድቁት ነው፡፡ እነሱ ሳያፀድቁት ተግባራዊ አይሆንም ተብሏል፡፡ ጉዳዩ ቤት፣ ንብረት እስከ ማቃጠል፣ ሰላማዊው ህዝብ ላይ ሁከት እስከመፍጠር የሚያደርስ አልነበረም፡፡ ይሄ በምትገኘው ቀዳዳ ብጥብጥ በማነሳሳት፣ በብጥብጡ መሃል ተጠቃሚ ነኝ ብሎ የሚንቀሳቀስ ሃይል የሚሠራው ነው፡፡ 
በዩኒቨርስቲዎቹ የተከሰተው የጐሳ ግጭት የፌደራሊዝም አወቃቀሩ የፈጠረው ቀውስ ውጤት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እኒህ ወገኖች፤ አዲሱ ትውልድ የተቀረፀው “እኔ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከትግሬ” በሚለው አስተሳሰብ ነው ሲሉም ይሟገታሉ…
አሁን የተከሰተው ችግር ኢህአዴግ የፈጠረው ነው፤ የዘራው ዘር ውጤት ነው የሚሉ አሉ፡፡ የብሔር ብሔረሰብ ጉዳይ እንቅፋት የሚሆነው መብቱ ባይከበር ነው፡፡ ኢህአዴግ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ኢትዮጵያ ውስጥ በአግባቡ ካልተከበረ፣ ኢትዮጵያ የትርምስ አገር ትሆናለች ብሎ ነው የሚያምነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ሙሉ በሙሉ፣ በአስተማማኝ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ ህገ-መንግስታዊ ምላሽም አግኝቷል፡፡ ነገር ግን ሰበብ ነው የሚፈለገው፤ ስስ ብልትን የመጠቀም ጉዳይ ነው፡፡ በሀይማኖትና በብሔረሰብ ህብረተሰቡን ከቀሰቀስነው በቀላሉ ይነሳሳል ተብሎ ስለሚታሰብ፣ አጀንዳዎቹ ብሔር ብሔረሰቦችና ሃይማኖት ላይ ያነጣጥራሉ፡፡ 
ብሔርህ ተሰደበ በሚል ዲሞክራሲያዊ ማንነትህ ተረገጠ እያሉ የሚያነሳሱ አሉ፡፡ ይሄን ደግሞ ህዝቡ ይረዳል፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በአብዛኛው ያበረደው እኮ ህብረተሰቡ ነው፤ የብሔር እኮ ቢሆን ምንም ማድረግ አይቻልም ነበር፡፡ 

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል የሚል አቤቱታ ዘወትር ያሰማሉ፡፡ ኢህአዴግና መንግስት ምን ይላሉ?
የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡን፤ አባላቶቻቸው እየታሰሩባቸው መሆኑን፤ ሁሌም ሲናገሩ ይሰማል። ነገር ግን ሠላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ በየትም ሀገር የራሱ ደንብና ስርአት አለው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ከስሙም እንደምንረዳው በሰላማዊ ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን መግለፅ ነው፡፡ ኢህአዴግም ሰላማዊ ሰልፍ ላድርግ ቢል በተመሳሳይ ደንብና ሥርዓት ነው የሚስተናገደው፡፡ ምህዳሩ ጠቧል የሚለው የተለመደ አባባል ነው፡፡ ኢህአዴግ፤ አባል አትመልምሉ አላለም፡፡ አባል መመልመል፤ ፖሊሲን ማሳወቅ፤ ለህዝብ አቅርቦ በፖሊሲ መመረጥ አልተከለከለም፡፡ ይሄን አታድርጉ ከተባለ ምህዳሩ ጠቧል ማለት ይቻላል፡፡ 

ምርጫ ማለት የፓርቲዎች መቀያየር አድርገው የሚቆጥሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በዚህ ዓመት ኢህአዴግ ይመረጣል፣ በሚቀጥለው ሌላው ይመረጣል ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ ይሄ ካልሆነ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ አይደለም ብለው ይደመድማሉ፡፡ በተደጋጋሚ ምርጫ እያሸነፉ የዘለቁ ብዙ ዲሞክራሲያዊ አገሮች አሉ፡፡ ህንድ፣ ጃፓን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አውሮፓ ውስጥ፣ በአሜሪካ ስቴቶችም አሉ፡፡ ከ40-50 ዓመት ስልጣን ይዘው የቆዩ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ይሄ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ሲመጣ ለምንድነው ዲሞክራሲያዊ የማይሆነው? ስለዚህ የአውራ ፓርቲ ሥርዓት (ዶሚናንት ፓርቲ ሲስተም) የዲሞክራሲዊ ምርጫ ውጤት ነው፡፡ ህዝቡ ከዚህ የተሻለ ልማት፣ ዲሞክራሲ፣ ፍትህ… ይፈልጋል፡፡ ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ነው መፈተሽ ያለባቸው፡፡ ኢህአዴግን ከሚወቅሱ ራሳቸውን ይጠይቁ፡፡    

 

Source/www.addisadmas.com

Posted by/Lemlem Kebede 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s