የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በወር 15ሺህ ዶላር ደመወዝ ፖርቱጋላዊ አሰልጣኝ ቀጠረ

 

በመንሱር አብዱልቀኒ – በኢትዮስፖርት ጋዜጣ ላይ ታትሞ የወጣ)

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጠዋት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሾሙን የሚገልጹ መረጃዎች ከወጡ በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፈጥኖ ማስተባበያ ልኳል፡፡ ረፋዱ ላይ የሹመቱ ዜና እንደተነገረ ከቀትር በኋላ የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ተከታታይ የማስተባበያ ፕሬስ ሪሊዞች በትኗል፡፡ ፌዴሬሽኑ የቀድሞውን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስፖርት አምድ አዘጋጅ አቶ ወንድምኩን አላዩን በህዝብ ግንኙት ኃላፊነት መሾሙ ይታወቃል፡፡ በአቶ ወንድምኩን የግል ኢሜይል አድራሻ በኩል የፌዴሬሽኑ ኦፊሴላዊ መግላጫዎች፣ ዜናዎችና ጥቆማዎች ለመገናኛ ብዙሃኑ በኢሜይል ይላካሉ፡፡ ከአቶ ወንድምኩን ሹመት በፊትም በሚድያው አባላት ዘንድ ክብርና ተወዳጅነትን ያተረፈችው ወይዘሮ ዘውድነሽ ይርዳው የተቋሙን የህዝብ ግንኙነት ክፍተቶች በብቃትና በታታሪነት ስትሸፍን ትልቁ የመገናኛ መሳሪያዋ ኢሜይል ነበር፡፡ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ቢዘጋጅ ወይም ተቋሙ የሚልከው ሰበር ዜና ቢኖር አንድ ጋዜጠኛ በሞባይል ስልኩ በኩል ባለበት ቦታ መልዕክቱ ይደርሰዋል፡፡

ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ የግል ስልኬ ደጋግሞ ምልክት ይሰጠኝ ነበር፡፡ ከፊሉ በዕለቱ ለንባብ የበቃችው ኢትዮ-ስፖርት በርዕሰ አንቀጿ ስለሰጠችው ጥቆማ የሚናገሩ መልዕክቶች ሲሆኑ አራቱ ደግሞ ከአቶ ወንድምኩን አላዩ የተላኩ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬስ ሪሊዞች ነበሩ፡፡ የህዝብ ግንኙነቱ ክፍል በዕለቱ በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን የመረጃ ግርታ ለማጥራት በተከታታይ ማብራሪያዎችንና ማስተካከያዎችን ያከሉ መግለጫዎችን ልኳል፡፡ ፈጥኖ መረጃን ማስተካከል እጅግ ዘመናዊነት በመሆኑ አቶ ወንድምኩንና ዴፓርትመንታቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

ፌዴሬሽኑ ደጋግሞ እንዲያስተባብልና ብዥታውን እንዲያጠራ የተገደደበት ምክንያት የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሹመት ከፍተኛ የህዝብ ትኩረት በመሆኑ ነው፡፡ ተሹዋሚውን መምረጥ እንደቀድሞው ቀላል አይደለም፡፡ ከሚድያውም ሆነ ከህዝቡ ብዙ ጥያቄዎችን ያስከትላል፡፡ የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድን በአፍሪካ ዋንጫና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ባሳየው እመርታ የዋልያዎቹ ነገር ዓብይ የህዝብ ትኩረት ሆኗል፡፡ መገናኛ ብዙሃንም ተሹዋሚው ማን የመሆኑን ዜና ለህዝብ የማሳወቅ የጓጉትም ለዚህ ነው፡፡

በሚድያውና በህዝቡ ትኩረት ምክንያት ፌዴሬሽኑ የአሰልጣኙን ሹመት ይፋ ለማድረግ ጫና ውስጥ ሳይገባ አልቀረም፡፡ በእርግጥ ብሔራዊ ቡድን ያለአሰልጣኝ መቆየት አይገባውምና ፈጥኖ ቢሾም መልካም ነበር፡፡ ይህኛው ጫና ግን ከዚህ አንጻር ሳይሆን የህዝቡና የሚድያው ጉጉት ከማየሉ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

የህዝብ፣ የመንግሥት እና የፌዴሬሽኑ ትኩረት ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የሚገኝ አሰልጣኝ መቅጠር ላይ ብቻ ካተኮረ ግን ስህተት ነው፡፡ በፌዴሬሽኑ አካባቢ ያሉ ታማኝ ምንጮች ለኢትዮ-ስፖርት እንደገለጹት መንግሥትም ሆነ ፌዴሬሽኑ ብሔራዊ ቡድኑን ከቀደሙት ስኬቶች በላይ ሊያደርስ ይችል ዘንድ የታመነበት አሰልጣኝ መሾሙ ላይ አተኩረዋል፡፡ በዚህ ረገድ የመንግሥትም እርዳታ መኖሩ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ዘመናዊ ጎዳናን ለመከተል ዘመናዊ አስተሳሰብ ያለው አሰልጣኝ ጠቃሚነቱ አያጠራጥርም፡፡ ሆኖም ዘመናዊነት ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፈለው አሰልጣኝ መቅጠር ብቻ አይደለም፡፡ በብሔራዊ ቡድኑ ቴክኒካዊ አስተዳደር ላይ በግልጽ የሚታይ ለውጥ ካልኖረ አንድን ባለሙያ ብቻ መሾም ፍሬ አይኖረውም፡፡

ለምሳሌ፡- በወር 20ሺህ ዶላር የሚከፈለው አሰልጣኝ ሊቀጠር ይችላል፡፡ የቅጥሩን መመዘኛ አሟልቷል የተብሎ የሚሾመውን ባለሙያ ደመወዝ መክፈል ብቻ የዕድገቱ መንገድ አይሆንም፡፡ አሰልጣኙ በዘመናዊው የእግር ኳስ ዓለም ውጤታማ አሰልጣኞች ሊያገኙ የሚገባውን ድጋፍ ከፌዴሬሽኑና በዙሪያው ካሉ የብሔራዊ ቡድኑ የስልጠና ባልደረቦቹ የሚያገኝበት ሜዳ የተጠረገ ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ የአመለካከትና መሰረታዊ የአሰልጣኞች ስታፍ መዋቅራዊ ተሃድሶ እንደሚያስፈልገው ደፍሬ እናገራለሁ፡፡

ቀጣዩን የብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት የቡድኑ የቴክኒክ አስተዳደር የሚሻሻልበት ኦፊሴላዊ ፕሮፖዛል ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ወይም ለሚመለከተው አካል ቢያቀርቡ መልካም ነው፡፡ አዲሱ ተሹዋሚ ከዘመኑ እግር ኳስ ጋር የሚራመድ እስከሆነ ድረስ ለውጤታማነቱ ዘመናዊ አሰራርን ገቢራዊ ለማድረግ የተዘጋጀ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ያረጀውንና በብሔራዊ ቡድኖቻቸው የተለመደውን አሰራር አሽቀንጥሮ ለመጣል ማመንታት የለብንም፡፡ አዲስ አቀራረብ ብሔራዊ ቡድኑን ለበለጠ ውጤት ለማድረስ እንደሚበጅ አምነን ከዘመኑ ጋር ለመራመድ መዘጋጀት አለብን፡፡

ረዳቶች

የ20 እና የ30ሺህ ዶላር አሰልጣኝ ብልህ ረዳቶችና ከረዳቶቹም ጋር ለውጤታማነት የሚሰራበት ሲስተም ይፈልጋል፡፡ ምክትል አሰልጣኝ ለመሾሙ ነገር በዋና አሰልጣኙ መልካም ፈቃድ እንጂ በፌዴሬሽኑ ብቸኛ ጥቆማ ከተወሰነ የስህተቱ መጀመሪያ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ተሹዋሚው ረዳቱን የመምረጡ አብላጫ የመወሰን ድምጽ ሊነጠቅ አይገባም፡፡ ምን ያህል ረዳቶች እንደሚያስፈልጉት መወሰንም የተሹዋሚው ውሳኔ መሆን አለበት፡፡ አዲሱ አሰልጣኝ በውሳኔዎችና በዕቅዶች ላይ ተጨባጭ መነሻና ምክንያት ያላቸውን ብሩህ ረዳቶች (ከተሟላ የስራ መመሪያ ጋር) ይፈልጋል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ የተጫዋቾች ምርጫ በቀደመ ዝና እና ባለፈ ረከርድ የመሆኑ አሮጌነት አብሮን ሊጓዝ አይገባም፡፡ ለአከራካሪ ምርጫዎች ጥልቅ ትንተና ያስፈልገናል፡፡ የቪዲዮ ማስረጃዎችና ትንተናዎች በዘመኑ እግር ኳስ ደጋፊ ናቸው፡፡ ከሹመቱ ጋር ተቋሙ የአሰልጣኞች ስታፉ ከጠለቀ እይታና ትንተና በመነሳት የቡድን ግንባታ ሂደቱን የሚፈጽም እንዲሆን አመቺ ከባቢ መፍጠር አለበት፡፡ ብሔራዊ ቡድን ብሔራዊ ምልክት እንደመሆኑ በኮስታራ አስተዳደር ስር መግባት ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችን ለቡድኑ ምርጫ ለማብቃት ብቃታቸውን ለመገምገምና ካስፈለገም ለትውልድ ሃገራቸው እንዲጫወቱ ለማግባባት አሰልጣኞች ወደየትም ሃገር መጓዝ እንዲችሉ በፋይናንስ ምክንያት መገደብ የለባቸውም፡፡ ዋና አሰልጣኙ በአዲስ አበባ በሚደረጉ የሊግ ጨዋታዎች ላይ ቢያተኩር እንኳን በክልል የሚደረጉ ግጥሚያዎችን ለመገምገም ረዳቶቹን ለመላክ የፋይናንስና የቢሮክራሲ አፈጻጸም ዝግጁነት ያስፈልገዋል፡፡ እገሌ የተባለውን ረዳት ወደ ሐረር ወይም አርባ ምንጭ ለመላክ ዋና አሰልጣኙ መቸገር የለበትም፡፡ ነገ ዛሬ ሳይባል ለተልዕኮው የትራንስፖርትና የሆቴል ወጪው ሊሸፈንለት ያስፈልጋል፡፡ ረዳቱም ከዋና አሰልጣኙ በሚሰጠው መስፈርት መነሻነት ገምግሞ እንደነገሩ ገጽ የሞላ ፍሬ የለሽ ጽሁፍ ማቅረብ የለበትም፡፡ በቴክኒክና ታክቲካዊ ነጥቦች የጠለቀ፣ አሳማኝ ጥቆማና የተብራሩ ትንተናዎችን በማቅረብ በቦታው ላልተገኘው ዋና አሰልጣኝ ያልተዛነፈ ማስረጃ ካላቀረበ ትርፉ ድካምና ወጭ ብቻ ይሆናል፡፡

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚዎች ለጥልቅ ትንተና በሚያመች መልኩ ጨዋታዎቻቸውን ገምግመው አያውቁም፡፡ ሶስት አራት ጊዜ የጨዋታዎችን ቪዲዮ መመልከትና እርግጠኛነት የጎደላቸው በወፍ በረር የተለኩ መረጃዎችን ማቅረብ ጊዜ አልፎባቸዋል፡፡ የሱዳኑ ሂላል ክለብ ሁለት የቪዲዮ ተንታኞች እንዳሉት አውቃለሁ፡፡ ሁለቱ ባለሙያዎች የአሰልጣኝነት ማዕረግ ያላቸው አለመሆናቸው ለሃገራችን እግር ኳስ አስገራሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ከፍ ካለም የጨዋታዎች ትንተና የደረሰበትን ርቀት መመልከት እንችላለን፡፡ ሪያል ማድሪድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ባደረገው የስፔን ጥሎ ማለፍ ዋንጫ የደርሶ መልስ ጨዋታ በአሰልጣኙ (በብቁ ረዳቶች ድጋፍ ማግኘታቸውን አትዘንጉ) የቀረበው የቴክኒካዊ ግምገማ ሪፖርት ባለ 73 (ሰባ ሶስት) ገጽ ነበር፡፡ ፔፕ ጋርዲዮላ በባርሴሎና ኃላፊነቱ ወቅት ለአንድ ጨዋታ 93 (ዘጠና ሶስት) ገጽ ሪፖርት ማቅረቡን አውቃለሁ፡፡ ቁጥሮቹን በአሃዝና በፊደል የጻፍኩት ምናልባት አንባቢ የትየባ ስህተት ተፈጽሞ እንደሆነ እንዳይጠራጠር በማሰብ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ በድን በሪያል ማድሪድና ባርሴሎና ደረጃ መታየት አለበት እያልኩ አይደለም፡፡ ደረጃችን የሰማይና የምድር ያህል መለያየቱን አልክድም፡፡ የዘመኑ እግር ኳስ የቡድን ዝግጅት የት እንደደረሰ ለመጠቆም ፈልጌ ነው፡፡ የዋልያዎቹ ነገር እንደ አቅሙ ከዘመኑ ጋር መራመድ ካለበት ግን የራሱን ተጨማሪ የዕድገት ርቀት መጓዝ ግዴታው ይሆናል፡፡

የአካል ብቃት ዝግጁነት፣ ተደጋጋሚው ጩኽት

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ የአካል ብቃት እና የጉዳት መከላከል ዝግጁነት ነው፡፡ ተደጋግሞ እንደተነገረው ካለፈው ተሞክሯችን መነሻነት ብሔራዊ ቡድኑ የአካል ብቃት አሰልጣኝ ይፈልጋል፡፡ የ20ሺህ ዶላሩን አሰልጣኝ ሁሉን ለብቻው እንዲሰራ በኮንትራት ውሉ ላይ ልናስገድደው አንችልም፡፡ ብቻውን ሊሰራ ውል የሚፈጽም አሰልጣኝ ቢኖር እንኳን በሌላ ቦታ በቂ የስራ ዕድል የሌለው ብቻ ነው፡፡ ኮስታራ ባለሙያ በሁሉ ረገድ ፕሮፎሽናል አቀራረብን ይከተላል፡፡ 10 ድስት ጥዶ አንዱም የማይበስልለት አይደለም፡፡ እንደ አሰልጣኞች ስታፍ አለቅነቱ በነገሮች የመወሰን መብት ያለው መሆኑን የሚያውቅ መሪ በተግባር ክፍፍል ያምናል፡፡ እግር ኳስ በሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን በአሰልጣኞች ስታፍ ውስጥም የቡድን ስራ ነው፡፡ ዘርፉ የአካል ብቃት ላይ ብቻ እውቀትና አንጻራዊ ስኬታማ ተሞክሮ ያለውን ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ክለቦቻችን በዚህ የዘመናዊነት እርከን ላይ የመራመድ ባህል ስለሌላቸው ብሔራዊ ቡድኑም በተመሳሳይ አሰራር ስር ሲንገታገት ኖሯል፡፡ የምንገጥመውን ቡድን ጠንካራና ደካማ ጎን ለማወቅ መትጋት ያለብንን ያህል ተጫዋቾች ተሰጥኦዋቸውን በሜዳ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳቸውን ሙሉ የአካል ብቃት ሁልጊዜ ማግኘት አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ በመስኩ ባለሙያ ብቻ የሚሰራ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ አመራሮች ለዚህ ሃሳብ ጀርባቸውን መስጠት የለባቸውም፡፡ ፉትቦል አካላዊም ስፖርት መሆኑን መዘንጋት መሳሳት ነው፡፡

የፕሬስ አታሼ ነገር

ብሔራዊ ቡድኑ የራሱ የሆነ የፕሬስ አታሼ ይፈልጋል፡፡ ለቡድኑ ውጤታማነትን የሚመኝ አመራር በቡድኑና በህዝቡ መካከል ያሉትን መገናኛ ብዙሃን በዘመናዊ ስርዓት ማገናኘት አለበት፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅትና ጨዋታ በሚኖሩት ጊዜ በዙሪያው የሚወጡትን መረጃዎች ለሚድያው የሚያቀብል፣ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን የሚያዘጋጅ፣ መዘጋጀታቸውን ለሚያድያው የሚያሳውቅ፣ የሚድያውን አባላት የሚያስተናግድ፣ ለአንድ ለአንድ ቃለምልልሶች የሚያስተባብርና ከላይ በተጠቀሱት ወቅቶች ቡድኑን በተመለከተ በራሱ ቃለምልልሶችን የሚሰጥ የፕሬስ አታሼ ያስፈልገዋል፡፡ የፕሬስ አታሼ እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አንድ አይደሉም፡፡ የፕሬስ አታሼው የብሔራዊ ቡድኑ ጉዳይ ብቻ የሚመለከተውና ሹመቱም ከቡድኑ ጋር የተሳሰረ ባለሙያ ነው፡፡ ቡድኑ በሄደበት ሃገር ሁሉ አብሮ ይጓዛል፡፡ የቡድኑ አንድ አባል የሚያገኘውን ጥቅምና መስተንግዶ ሁሉ በማግኘት ይሰራል፡፡ እግር ኳስ ተጫዋቾች ከልምምድ በኋላ ለማዕድ ይሰበሰባሉ፡፡ ከዚያም ዕረፍት ይወስዳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም እንደታየው በማረፊያ ሰዓታቸው ሚድያውን ለማስተናገድ ሊገደዱ አይገባም፡፡ በጋዜጠኞች የስልክ ጥሪ መረበሽ የለባቸውም፡፡ ይህ ለአሰልጣኞቹም ይሰራል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በዚህ ረገድ የደረሰባቸውን አለመመቸት ያውቁታል፡፡ ተጫዋቾችም እንዲሁ፡፡ ያለፈውን ስህተት በመማሪያነት በመጠቀም እርምት ያስፈልገናል፡፡

ተጫዋቾች ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ያላቸው የስራ ግንኙነት ቢያንስ የህዝብ በሆነው ብሔራዊ ቡድን ስርዓት መያዝ አለበት፡፡ በቡድኑ ዙሪያ በየዕለቱ የሚፈጠሩ አዳዲስ ጉዳዮችም ስርዓትን በጠበቀና የቡድኑን የዝግጅት ትኩረትና ዕረፍት ባላሳነሰ መልኩ ለሚድያው መድረስ ይኖርባቸዋል፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት ከሁለት ሬዲዮ ጣቢያዎችና አንድ ቴሌቪዥን በስተቀር አልነበረንም፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባ ብቻ ሶስት ቴሌቪዥን እና ስድስት ሬዲዮ ጣቢያዎች አሉን፡፡ በየክልሉም ተበራክተዋል፡፡ ለእግር ኳሱ ሽፋን የሚሰጡ በርካታ ጋዜጦችና መጽሔቶችም አሉ፡፡ የሙዚቃና የመዝናኛ ሬዲዮ ፕሮግራሞች ለእግር ኳስ መደበኛ ሽፋን መስጠታቸው ተለምዷል፡፡ በዋና ጸኃፊነት እንደማገለግለው የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር እይታ ከ100 በላይ የስፖርት ጋዜጠኞች በመላው ሃገሪቱ ይገኛሉ፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ የፕሬስ አቀራረብ ግን ከ20 ዓመት በፊት በነበረበት አቋም ላይ እንዳለ ነው፡፡ ይኽው አመለካከት ተሃድሶ ይፈልጋል፡፡ ከዘመኑ ጋር መራመድ ይኖርበታል፡፡ በእግር ኳሱ ዓለም ውጤታማነት የተለያዩ ሚናዎች ውህደት እንጂ የአንድ አሰልጣኝ ብቃት ብቻ አይደለም፡፡ ዋና አሰልጣኙ የነገሮች ሁሉ የበላይ አለቃ እንጂ የነገሮች ሁሉ ፈጻሚ ሊሆን አይችልም፡:

ምንጭ – ኢትዮ-ስፖርት ጋዜጣ (ከሃገር ቤት)

Posted by/Lemlem Kebede

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s