አስገራሚው የሳውዲው “ኮራጅ ” አባት ምክር እና የኢትዮጵያ ሰርከስ መስራች በሳውዲው ስደት !

አስገራሚው የሳውዲው “ኮራጅ ” አባት ምክር

       ነገሩ እንዲህ ነው …ከ20 ዓመት በፊት ሳውዲው ወጣት ራሱን ለሁለተኛ ደረጃ ፈተና ከማዘጋጀት ይልቅ በረቀቀ መንገድ ለፈተናው መልስ የሚሆነውን ማጭበርበሪያ የመልስ ወረቀት አዘጋጅቶ ለፈተና ይቀርባል። ፈተናውን በረቀቀ መንገድ አጭበረብሮ ሰርቶታልና ፈተናውን በተገቢ ውጤት አልፎ ከፍተኛ       የትምህርት ተቋም ለማለፍ በቃ ! ከዚያም በታዋቂው ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ተከታትሎ ይመረቃል። ይህ ሁሉ አልፎ ስራ ይዞ እና ጎጆ ቀልሶ ለወግ ለማዕረግ በቃ !  ከጎጆም  አልፎ  የሰመረው ህይወቱ የልጆች አባት እስከ መሆን ታደለ  !

    በያዝነው ሳምንት የድሮው ተማሪና የዛሬው አባወራ ጆሮውን ያልተለመደና የማያውቀው ህመም ያሰቃየው ገባ ። ወደ ሃኪም ቤት ጎራ በማለት ምርመራ ሲያደርግ ለህምሙ ዋና ምክንያት በጀሮው ውስጥ ቁራጭ ወረቀት እንደሆነ የሚያስረዳው አስገራሚው ውጤት ተነገረው …  አረጋዊው አባት በወጣትነት እድሜው ተግቶ በማጥናት ለፈተና ቀርቦ ማለፍ ሲገባው  አስነዋሪ የማጭበርበር ድርጊት መፈጸሙን እያስታወሰ አልተደሰተም ፣ አዘነ እንጅ  ! ዛሬ ለማጭበርበሩ የተጠቀመበትን ወረቀት በጀሮው እንዴት ሊያስገባው እንደቻለ ማመን ቢያዳግትም ከ20 አመታት በፊት     ለኩረጃ እና ለማጭበርብር የተጠቀመበት  ወረቀት በቀዶ ጥገና ከጀሮው እንዲወጣ መደረጉ አስገራሚውን ዜና     እየተቀባበሉ እየዘገቡ ካሉት የአረብ መገናኛ ብዙሃን ለመረዳት ችያለሁ … !       ከሁሉም የሚያስገርም የሚያስደስተው በሰራው ስራ የሚያፍር እንጅ የማይኮራው አባት ልጆቹንና ወጣቶችን       ሲመክር  “ልጆቸ ሆይ ፈተና ለማለፍ አታጭበርብሩ! ” ማለቱ ተጠቅሷል ። የትናንቱ ተማሪ የዛሬው አባወራ ሳውዲው  አባት በሰራው ስራ ተጸጽቶ ቀሪውን ለመምከር ወደ አደባባይ መውጣቱ ቢያስደስተኝ በዝንቅ መረጃየ ስር መረጃውን  ላካፍላችሁ ፈቀድኩ !

      ሳውዲውን አባት መልካም ምክር ካነሳሁ አይቀር ሰሞነኛ የማለዳ ወጌ  እንግዳ ለማድረግ ስለፈቀድኩት አንድ ከ20 አመት በፊት በኢትዮጵያ   ሰማይ ስር ባንድ ወቅት አንቱ የተባለ ስም ስለነበረው ብርቱ ወንድም    ላጫውታችሁ … አብደላ አህመድ ኦመር ይባላል ። ቀዳሚው የኢትዮጵያን ሰርከስ መስራች ነው ። በስራው   ቻይናን ጨምሮ በርካታ ሃገራትን ጎብኝቷል … ብርቱ ስፖርተኛ  ከመሆን ባለፈ አንድን ሙያ ልያዝ ብሎ ከተነሳ በፍጥነት ክህሎትን የማዳበር ልዩ ተፈጥሮ ያለው ወንድም እንደሆነ ሰምቻለሁ !    ዛሬ  በእርግጠኝነት መናገር  የምችለው ነገር ቢኖር ብዙሃን ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ሰርከስ መስራች ማን እንደሆነና የት  እንዳለ የሚያውቁ አይመስለኝም  !  … ብርቱው የቀድሞው ስፖርተኛ እና  የሰርከሱ መስራች አብደላ  ግን ሳውዲ አረቢያ ጅዳ ትዳር መስርቶ እና ልጆች ወላልዶ በስደት ህይዎትን በመግፋት ላይ ነው ።

  አብደላን ሳላውቀው… ላውቀው!

መልከ መልካምና ደልዳላ ተክለ ቁመና ካለው ወንድም ጋር ለአመታት ልጆቸን በማስተምርበት በጅዳ የኢትዮጵያውያን አለም አቀፍ ትምህርት ቤት እንተያያለን ፣ ግን አንተዋወቅም ። በአንድ ወቅት ከአንድ       ወዳጀ ጋር የትምህርት መለቀቂያ ሰአት ደርሶ ልጆቻችን ስንጠባበቅ    አብደላ  ሰላምታ   አቅርቦልን አለፈ … አብደላን አንድ ወዳጀ ያውቀው ነበርና እንዲህ አለኝ … ” ለመሆኑ ይህን ሰው ማን እንደሆነ ታውቀዋለህ? ” ሲል ጠየቀኝ አረ አላውቀውም ስል መለስኩለት … ” አየህ ሳውዲ ያልያዘችው ፣ ያላቀፈችው ሃበሻ አይነት የለም፣ አንተ   ደግሞ የሩቅ የሩቁን ፣ በበርሃ የምታገኘው ዘፋኝና ግፉዕ ተምር ለቃሚ ግመል ጠባቂ እህቶችን እንጅ እንዲህ በቅርብ ያለውን አየታይህም “   ሲል የመሰለውን አስተያየት ሲሰነዝር እንደ መቀለድ እያለ በፈገግታ   ተሞልቶ ነበር እና እኔም እንደመሳቅ አልኩ ! ወዳጀ ወጉን ቀጠለ …

   ” አንደላን በትንሹ ከአስራ አምስት አመት በላይ አውቀዋለሁ። ስፖርተኛ ፣ አስማተኛ ፣ የስነ ጽሁፍ ክህሎትን የተካነ   በሁሉም የሙያ መስክ የምታገኘው ሰው ነው። ዛሬ እንዲህ አንገቱን ደፍቶ ፣ ሰውነቱ ገዝፎ ስታየው የዋዛ አይምሰልህ (ፈገግ ብሎ) ፣ ከበርካታ አመታት በፊት ታዋቂው የአካል እንቅስቃሴ አሰልጣኝ ግርማ ቸሩ ለአመታት በአሰልጣኝነት    ይሰራባቸው ከነበሩ በወቅቱ ታዋቂ ቱጃር በነበሩት የሸህ አልዙማን ስራ ተሰናብቶ ሳውዲን ሲለቅ የተተካው ፈርጣማው ጎልማሳ አብደላ ነበር ። ከዚያም የባለጸጎቹን ቤተሰቦች በአካል እንቅስቃሴ አሰልጣኝነት እና በልዩ ጥበቃ ለአመታት     በመስራት ያልዞረበት ሃገር የለም ።  በአዕምሮው በሳል ፣ በአካል ፈርጣማ ስፖርተኛ ነው ። አየህ ነቢዩ በሳውዲ ስደት የታቀፈው ግፉአን እህቶችና ወንድሞች ብቻ አይደሉም። እንዲህ አይነት ባለሙያም ሳውዲ ውስጥ ይኖራል። ታሪኩን  ለመናገር ፈቃደኛ ከሆነ ለቀረው ትውልድ አስተማሪ ነውና  አንድ ቀን አስተዋውቅህና  እንዲያጫውትህ አደርጋለሁ! “   አለኝ ።  … አብደላን ሊያገናኘኝ ከአንድ አመት በፊት እንዲህ ቃል የገባልኝ ቅን አሳቢ ወንድም ግን ዛሬ ከአካባቢው የለም …  ኑሮው ቢከብደው ቤተሰቦቹን ይዞ እና ጥሪቱን አጠረቃቅሞ የአቅሙን ያህል ለመስራት ሃገር ቤት ገብቷል  … ካንድም ሁለት ሶስት ጊዜ በፊስ ቡኩ መስመር ብንገናኝም ሃገር ገብቶ የሚይዝ የሚጨብጠው እንዳጣ መረጃ የሚያቀብለኝን ወንድም” አብደላን አገናኘኝ?” ብየ ማስቸገሩ ከብዶኝ መክረሙ እውነት ነው!     መቸም ዘንድሮ መንገድና ፊስ ቡክ የማያገናኘው የለም ፣ የኢትዮጵያውን ሰርከስ መስራች በቀጭኑ የስልክ     መስመር በሌላ ጉዳይ አግኝቸው ስናወጋ ማንነቱን ሲያጫውተኝ ማመን አልቻልኩም ። ፎቶዎችን ፣ ሰነዶችን በመረጃ ማስረጃነት  ሲያጋራኝ ግን የማይታመነውን አጋጣሚ ለማመን ተገደድኩ  ! ከወንድም አብደላ ጋር ልንገናኝ ቀጠሮ ይዘናል ። … በቀይ  ባህር ዳርቻዎች ከቤተሰቦቻችን ጋር ተገናኝተን ፣ ልጆቻችን ሲጨዋወቱ ነፋሻውን የባህር አየር እየማግን    የኢትዮጵያ ሰርከስ መስራቹን የአብደላን ዠንጉርጉር ህይወት እኔ እየጠየቅኩ እሱ በትዝታ እየነጎደ እስኪያወራኝ  ቸኩያለሁ …

መልካም ቀን

ነቢዩ ሲራክ  / የካቲት 2006 ዓም

Posted by/ Lemlem Kebede

Leave a comment